ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡ ደኖችን ለዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል ትኩረት ተደርጓል

ጋምቤላ፤ጥቅምት 29/ 2018 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡ ደኖችን ለዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ በክልሉ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡ የተፈጥሮ ደን ሀብቶችን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጉላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሯች ባየክ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ብዝሃ ህይወት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።


 

የጋምቤላ ክልልም ባከናወናቸው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች የማጃንግና የአኝዋሃ ዞኖች የተፈጥሮ ደኖች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በባዮስፌር ሪዘርቭ መመዝገባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡ ደኖች በውስጣቸው በርካታ የእንስሳት፣ የዕጽዋትና የውሃ አካላትን የያዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህ ሀብቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዩኔስኮ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡት የተፈጥሮ ደኖች የአየር ንብረት ሚዛንን በማስጠበቅ ለዘላቂ የግብርና ልማት የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ደን ሀብቶቹ ብዝሃ ህይወትን መያዛቸው በዘርፉ ለሚደረጉ ጥናትና ምርምር ስራዎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኮንግ ኛክ በበኩላቸው፥ እንደ ሀገር በዩኔስኮ እውቅና አግኝተው በባዮስፌር ሪዘርቭ ከተመዘገቡት ስድስት የተፈጥሮ ደኖች መካከል ሁለቱ በጋምቤላ ክልል እንደሚገኙ ተናግረዋል።


 

በመሆኑም የተፈጥሮ ደኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ በባዮስፌር ሪዘርቭነት ያገኙትን እውቅናና በውስጣቸው የሚገኙ የብዝሃ ህይወት ሃብቶችን በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እየተየሰራ ነው ብለዋል።

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በደን ሀብቶች ላይ ተጨማሪ የጥናት ስራዎችን በመስራት የዘርፉን ጥቅም የማሳደግና የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም