የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያስቀጥል እመርታዊ የዕይታ አቅም ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያስቀጥል እመርታዊ የዕይታ አቅም ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያስቀጥል እመርታዊ የዕይታ አቅም መፍጠሩን የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ስልጠና ተሳታፊዎች ገለጹ።
ፓርቲው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበትን አካታችና አቃፊ ምኅዳር በመፍጠር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ሥልጠና በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ከፍተኛ አመራር አባላቱም ከስልጠናው በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ስራዎችን ጎብኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ፤ ስልጠናው የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን በማጽናት የግብርና ኢንዱስትሪ ሽግግርን የሚያፋጥን ዕውቀትና ክህሎት የተገኘበት ነው ብለዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፣ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ማፋጠን የሚያስችል የአመራር ዕውቀትና ክህሎት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።
በቱሪዝም፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በኢንዱስትሪና ከተማ ልማትን ስራዎችም ተመጋጋቢ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጫ አቅሞች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር፤ የመደመር መንግሥት ዕይታ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያስቀጥል አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ሥልጠናም የኢትዮጵያን ዕድገት ለማስቀጠል የጠራ ግንዛቤን በመያዝ ወደ ተግባር የሚገባበት ዕውቀትና ክህሎት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በቱሪዝም፣ በገጠርና ግብርና ሽግግር፣ ኢንዱስትሪ፣ ከተማ ዕድገትና የልማት መስክ አንኳር ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ ዕውቀትና ግንዛቤ የተገኘበት መሆኑን አንስተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበትን አካታችና አቃፊ ምኅዳር በመፍጠር የኢትዮጵያና ዜጎቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የመስክ ምልከታቸውም የብልፅግና ፓርቲ ከቃል የተሻገረ ተጨባጭ ስኬት ያስመዘገቡ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑና ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ሠለሞን፤ በአዳማ የስልጠና ቆይታቸው በቱሪዝም፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በአንዱስትሪና ከተማ ልማት ወሳኝ የኢኮኖሚ ዕድገት መስኮች ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማላቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በስልጠናውም የሀገርን ሁለንተናዊ ዕድገት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ለመምራት ልምድና ተሞክሮ በመጋራት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን አጽንቶ የሚያስቀጥል አቅም የተፈጠረበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ አሊ፤ በስልጠናው ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና አህትማማችነትን በማጠናከር የኢትዮጵያ ህብረት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በስልጠናውም የበለጸገችና የዜጎቿ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ የአመራር ስምሪት የተሰጠበት መሆኑንም ገልጸዋል።