ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ጸጋዎች በማልማት ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ አቅም እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ጸጋዎች በማልማት ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ አቅም እተፈጠረ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ አመራር አባላቱም ከስልጠናው በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በወሳኝ የኢኮኖሚ የልማት መስኮች በከፍተኛ የለውጥ ምህዋር ውስጥ እየተጓዘች እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠናም የኢትዮጵያ የስኬት አቅጣጫ በዕውቀትና ክህሎት መምራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በተሳታፊ አመራሮች መካከልም ኢትዮጵያ በጸጋዋ ልክ ዕድገትና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ቁጭትና የልምድ ልውውጥ የተፈጠረበት መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።

በስልጠናውም በወሳኝ የኢኮኖሚ ልማት መስኮች የመደመር መንግስት ዕይታ በዘርፎች እመርታ ላይ ንድፈ ሃሳብን ከተግባር በማቀናጀት የኢትዮጵያን የዕድገት አቅጣጫ ያመላከተ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በጋምቤላ ክልል የአኝዋ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኝኬው ጊሎ፤ ስልጠናው የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ዕውቀትና አቅም የተገነባበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ዕድገት የተገኙ የዕውቀትና ክህሎት ተሞክሮዎችን ወደተግባር መቀየር የሚያስችል አቅም የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተሰባሰቡ ስልጠናው ተሳታፊዎችም ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማስጠበቅ ሀገራዊ ዕድገትን በማስቀጠል የበለጠ የእርስ በእርስ መተዋወቂይ መድረክ መሆኑም ገልጸዋል።

የአፋር ክልል የዳያስፖራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጋሳ ሁመድ፡ ስልጠናው የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የሚያረጋግጥ አቅም የተፈጠረበት ነው ብለዋል።


 

በቀጣይም በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ምርታማነት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ የተጋሩበት መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

በስልጠና እና የመስክ ምልከታውም የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ማፋጠን የሚያስችል ሕብረ ብሔራዊነት በማስጠበቅ የአመለካከትና የተግባር አንድነት ተግባቦት የተፈጠረበት መሆኑን አስረድተዋል።

በስልጠናው ላይ ሁሉም የክልልና ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባላት ተወካዮች መሳተፋቸውም ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጠናከር የጋራ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የወሊሶ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለማ ጋሩምሳ፤ በስልጠናውም ሀገራዊ አንድነትና የጋራ የልማት አፈፃጸም አቅሞች የተፈጠረበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ስልጠናው ኢትዮጵያ የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ ለማጽናት ልምድና ተሞክሮ የተጋሩበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታቸውም በንድፈ ሃሳብ ከወሰዱት ስልጠና ጋር የተዛመደ ተጨባጭ የልማት ስኬት እየተመዘገበ መሆኑን መሬት ላይ መመልከታቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም