ቀጥታ፡

የለውጡ መንግስት ለጎንደር በሰጠው ልዩ ትኩረት ከተማዋ ወደ ከፍታዋ እየተመለሰች ነው - የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- የለውጡ መንግስት ለጎንደር ልዩ ትኩረት በመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች ከተማዋን ወደ ቀደመ ከፍታዋ እየመለሰ እንደሚገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

ዋና አፈ-ጉባኤው በጎንደር ቆይታ ላይ በሰጡት አስተያየት ከተማዋ በርካታ ነገር እያላት ሁሉ ነገር ያጣች ነበረች ሲሉ ተናግረዋል።

ያለፉት መንግስታት እና መሪዎች ለከተማዋ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ሳያደርጉ መቆየታቸውንም አውስተዋል።

ጎንደር በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ እና ትላልቅ ከተሞች አንዷ መሆኗን ገልጸው በሀገር መንግስት ግንባታም ትልቅ ድርሻ እንዳላት አንስተዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎች እና የቱሪዝም ሀብቶች ገልጦ የማሳየት ሀሳብ እና ተግባር ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

ጎንደር ከተማ ያላት ታሪካዊ ሀብቶች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች መልማታቸውንና በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

ለበርካታ ዓመታት የዘገየው የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን አቅጣጫ ተከትሎ በተከናወኑ ስራዎች አፈጻጸሙ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

መገጭ የጎንደርን ህዝብ መሰረታዊ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚፈታ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ለከተማዋ ትልቅ የልማት አቅም እንደሆነ ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማን ጥንታዊነቷን በጠበቀ መልኩ የማልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህም ውስጥ የፋሲል ቤተ መንግስት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቤተ መንግስቱ በእርጅን ምክንያት ሊፈርስ ተቃርቦ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ ከፍተኛ በጀት በመመደብ በተከናወነው ስራ ፋሲል እንደገና ተወልዷል ነው ያሉት።

ቤተ መንግስቱ ቅርስነቱን ጠብቆ ለጎብኚዎች በሚመች ሁኔታ ጥገናው ተጠናቆ መመረቁ እንዳስደሰታቸው የገለጹት አፈ-ጉባኤው፤ ፋሲል ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ስራው ተከናውኖ የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ለመሆን መብቃቱን ገልጸዋል።

ፋሲል ከዘመናት በኋላ የጎንደርን ትንሳኤ የሚያሳይ ሆኗል ብለዋል።

በሌላ በኩል የጎንደር ተፈጥሯዊ ይዞታ በመጠበቅ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ገጽታ እንዲቀየር ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ከተሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ የሆነው የጎርጎራ ኢኮሎጅ የከተማዋን እምቅ ሀብት በተግባር መግለጡን ነው የተናገሩት።

አቶ አገኘሁ አክለውም ጣናነሽ ፪ የውሃ ላይ ትራንስፖርትን በማሳለጥ የቱሪዝም ፍሰቱን መጨመር እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

በጎንደር የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎች ከተማዋን ወደ ቀደመ ከፍታዋ የሚመልሷት መሆናቸውን አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም