የመገጭ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ሕብረተሰብ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ይሰጣል - ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የመገጭ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ሕብረተሰብ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ይሰጣል - ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- በመንግሥት ቁርጠኝነት ግንባታው እንደገና የቀጠለው የመገጭ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ሕብረተሰብ ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን የሥራ ሁኔታ መገምገማቸውን እና የታደሠውን የፋሲል ግቢ መመረቃቸው ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰጡት ማብራሪያ የመገጭ መስኖ ግድብ ተጓትቶ መቆየቱን አውስተው፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግሥት ቁርጠኛ ውሳኔ አሁን ላይ ሥራው በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን እና በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ በሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅም ለአካባቢው አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አረጋግጠዋል።
ይህን ተከትሎ የአርሶ አደሩ ብሎም የከተማ ነዋሪዎች ገቢ እንደሚጨምር ገልጸው፤ በሌላ በኩል የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚውሉ ምንጮች እንደሚኖሩትና ይህም የከተማዋን የመጠጥ ውኃ ሽፋን እንደሚያሻሽለው አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ግድቡ ትልቅ ስለሆነ የቱሪስት መስኅብ በመሆን እና የአካባቢውን ‘ኢኮሲስተም’ በማስተካከል ረገድ ይጠቅማል፤ ውብ አካባቢ ለመፍጠርም በእጅጉ ያግዛል ነው ያሉት።
እንዲሁም የአዘዞ መንገድ በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ሲጠናቀቅ የከተማውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በማሳለጥ ለነዋሪው የተቀላጠፈ ሥራ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራን በተመለከተም፤ በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት ሥራ ለከተሞች ትንሳኤ ነው ብለዋል።
በተለይ ለጎንደር የፋሲል መታደስ፣ የኮሪደር ልማቱ፣ የአዘዞ መንገድ ሥራና የመገጭ ግድብ ሲጠናቀቁ የቱሪስት ሳቢነቷን ይጨምራሉ፤ ለንግድ ብሎም ለልማት እንቅስቃሴዋ መሳለጥ ከፍተኛ ሚና ያበረክታሉ ብለዋል።
የፋሲል አብያተ መንግሥት የታሪካችን፣ የማንነታችን እና የሥልጣኔያችን መገለጫ ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ የአብያተ መንግሥቱ መታደስ ለክልሉ ሕዝብ ብሎም ለሀገራችን ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ከሥልጣኔ ማስረጃነት ባለፈ የቱሪስት መስኅብ በመሆን እያገለገለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ሲጠናቀቁ የክልሉን ልማት እና ሀብት የመፍጠር ዐቅም እንደሚሳድጉት አንስተዋል።