ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ትስስርን እና ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ አለው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ትስስርን እና ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው በአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ የባንክ ኦፕሬሽኖች ዳይሬክተር ክዋቤና አዪሬቢ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በይፋ አስመርቃለች።

ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጭ በመላክ ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ውህደትን እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአፍሪካ ኢምፖርት-ኤክስፖርት ባንክ የባንክ ኦፕሬሽኖች ዳይሬክተር ክዋቤና አዪሬቢ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ሃብት ካላቸው ትልልቅ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በአህጉሪቱ የበለጠ ለውጥ እንዲያመጡ ማገዝ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ በአህጉሪቱ ያሉ ትልልቅ ኢኮኖሚዎች በአካባቢው ባሉ ሀገራት ኢኮኖሚየዊ ትስስርን በመፍጠር አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ አመላክተዋል።

የህዳሴ ግድብ ትብብርንና የጋራ ብልጽግናን ለማስፋፋት ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ የሀይል ነፃነትን በማረጋገጥ አህጉሪቱ የምታደርጋቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለማፋጠን ከፍተኛ አቅም እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በምታደርገው ተሳትፎ በኢንዱስትሪ ልማትና በማምረቻው ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻል እንደምታሳይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኃይል ሀብቶችን በጋራ በማሰባሰብ ቀጣናዊ ውህደትን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል

የኃይል ነፃነት የትኛውም ሀገር ቀጣይነት ያለውን እድገት እንዲያረጋግጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በቂ የኃይል አቅርቦትን ሳያሟሉ አፍሪካን መለወጥ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ አይነት ፕሮጀክቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጹህና ታዳሽ ኃይል በማቅረብ ለቀጣናዊ ውህደት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ባንኩ የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር ሆኖ ለመቀጠል እና በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ለውጥ ውስጥ ለመሳተፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም