ቀጥታ፡

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ካፍ ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ደረጃውን የማሻሻል ሥራ እተከናወነ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ደረጃውን የማሻሻል ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን እንዲሁም ከተማዋን ለቱሪዝም ዘርፍ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ደረጃውን የማሻሻል ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ስታዲየሙ 52 ሺህ ተመልካቾችን መያዝ እንደሚችል ገልጸው፤ የወንበር መግጠምና የሳር ንጣፍ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አረጋግጠዋል።

የመብራት ዝርጋታን ጨምሮ ሌሎች የስታዲየም ውስጥ መሠረተ ልማቶችም በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትን መሠረት በማድረግ በባሕር ዳር ጣና ሐይቅ ዳርቻ እየተገነባ ያለው ፈለገ ግዮን ሪዞርት መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።

ሪዞርቱ ወደ ሥራ ሲገባ የከተማዋን ተሪዝም ከማነቃቃት ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በባሕር ዳር እያስገነባ ያለው የኢትዮ-ፌሪስ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት በጣና ሐይቅ ዳርቻ እየተከናወኑ ካሉ ሌሎች የልማት ሥራዎች ጋር ተደምሮ ባሕር ዳርን ወደ አዲስ የከተሜነት ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ ሚና ያበረክታል ሲሉም ገልጸዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም