ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

አርባምንጭ ከተማ ከመቻል ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው አርባምንጭ ከተማ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው መቻል በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

መቻል በሰባት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
 
በሌላኛው መርሃ ግብር ቦሌ ክፍለ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ቡድኑ በስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ በሊጉ ባደረገው አንድ ጨዋታ ሶስት ነጥብ በማግኘት ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ተሳትፎ ምክንያት የመጀመሪያ ሶስት ሳምንታት ጨዋታዎቹን አላደረገም።

ጨዋታዎቹ በተስተካካይ መርሃ ግብርነት ተይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም