ቀጥታ፡

 የአፈር እና ውሀ ጥበቃ ስራ ምርታማነታችንን አሳድጎልናል-አርሶ አደሮች

ጭሮ ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦ በአካባቢያቸው የተከናወነው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማስቻሉን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የገመቺስ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች ህብረተሰቡን ያሳተፈ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

በዞኑ የገመቺስ ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳሉት በቀደሙት ዓመታት ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በነበረ የተዛባ አሰራር ደኖች በመመንጠራቸውና የአፈር ለምነት በመቀነሱ ምርታማ አልነበሩም።


 

ሆኖም አርሶ አደሮቹ ችግሩን በመገንዘብም በአካባቢያቸው የተጎዳውን መሬት በአረንጓዴ አሻራ በማልማት መልሶ እንዲያገግም  ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው የወሌንሶ ቀበሌ አርሶ አደር መሀመድ ሐሰን፤ በተራቆቱ ተራሮች ላይ በበጋው ወቅት ባከናወኑት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በክረምት አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በማከናወናቸው የአፈር ለምነቱ በመጨመሩ ምርታማ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡


 

በተራሮቹ ላይ የተተከሉት ችግኞች የውሃ አማራጮች እንዲጎለብቱ ማድረጋቸውን ገልፀው የተገኘው ውጤት ቀጣይ በሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

ከዓመታት በፊት ገላጣ የነበሩ ተራሮችን በእርከን በማሰርና በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ በመሸፈን የአፈር መሸርሸር ችግርን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ መቻላቸውን የተናገሩት ደግሞ  የቀበሌው አርሶ አደር ነስሮ ኢብራሂም ናቸው፡፡


 

የአፈር ለምነት በመጨመሩ የግብርና ምርታማነታቸው እንዲያድግ በማድረጉ በዚህ ዓመት የተተከሉ ችግኞችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ እየሰሩ መሆናቸውን  ተናግረዋል፡፡

የገመቺስ ወረዳ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው በወረዳው ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወነ ባለው የአካባቢ ጥበቃ ስራ  የተራቆቱ  ተራሮች አረንጓዴ ለብሰዋል ብለዋል፡፡


 

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ፍጹም አማረ፤ በዞኑ 15 ወረዳዎች ባለፈው ክረምት በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላችው ችግኞች ከ112 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መተከላቸውን አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በራሱ ተነሳሽነት ለተተከሉት ችግኞች ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የገመቺስ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ረመዳን አብዱረህማን በበኩላቸው በወረዳው ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሸርሸርን በማስቀረት፣ የከርሰ ምድር ውሀ መጠንን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት አሳድገዋል ብለዋል፡፡


 

የአካባቢው የደን መጠን በመጨመሩም እንደ የደጋ አጋዘን እና ሌሎች የዱር እንስሳት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በመስኩ እየታየ ያለው ውጤት አርሶ አደሩ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ባለቤትነት ስሜት በአካባቢ ጥበቃ እና በችግኝ ተከላ ስራዎች ላይ እንዲሳተፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም