በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ956 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ956 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን ተከናውኗል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ሶስት ወራት ከ956 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ መከናወኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሩብ ዓመቱ ከ1 ነጥብ 934 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር እና ከ211 ነጥብ 348 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለገበያ መቅረቡም ተገልጿል።
የንግድ ፈቃድ የመስጠት እና የማደስ ስራ በበይነ መረብ መከናወኑ የንግድ ስርዓትን ለማዘመን እና አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ያግዛል፡፡
የኦንላይን ሥርዓቱ አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ ለተገልጋዮችም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድ መሪ ስራ አስፈጻሚ ሊቁ በነበሩ እንዳሉት፤የኦንላይን (E-Trade)አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በዚህ አገልግሎትም የንግድ ፈቃድ ምዝገባ፣ የውጭ ንግድ ማቀላጠፍ እና ትስስር እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
ይህም ቅልጥፍናን በመጨመር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ብሎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ956 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በቴክኖለጂ የተደገፈው አሰራር የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን እና አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡
ከመሰረታዊ የሸቀጥ አቅርቦት አኳያም በሩብ ዓመቱ ከ1 ነጥብ 934 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር እና ከ211 ነጥብ 348 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያ ከማስፋፋትና ደረጃቸውን ከማሻሻል አኳያም አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ አሁን ላይ 1 ሺህ 700 ገበያዎች በመላ ሀገሪቱ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግስትና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከላት መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች ተሞክሮውን በመጋራት በቀጣይ የእቅዳቸው አካል እንዲያደርጉት አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስቀረት በተደረገ የቁጥጥር ሥራ 57 ሺህ 212 ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም ጠቁመዋል።