ቀጥታ፡

የወል ትርክት ግንባታ ይበልጥ እንዲጠናከር ሚናችንን እንወጣለን -  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 

ወላይታ ሶዶ፤  ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ):- የወል ትርክት ግንባታ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሚናቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የወል ትርክት ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር ትውልድን በመፍጠርና ጠንካራ ሀገረ መንግስትን በመገንባት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለውም ተመልክቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤  የተለያየ ስብጥር ባለው ማሕበረሰብ ውስጥ የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን ማጠናከር ሰላምን በማፅናት ሁለንተናዊ ስኬትን ያስመዘገበች ብርቱ ሀገርን ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። 

የጋራ ምክር ቤቱ አባልና  ሰብሳቢ  ጎበዜ አበራ፤  ኢትዮጵያውያን ከሚለያዩን ይልቅ የሚያቀራርቡን ነገሮች ይበዛሉ ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊነት ላይ የተገነባች ሀገር ብትሆንም ከዚህ ቀደም ሲነዙ የነበሩ ከፋፋይ ትርክቶች አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆኑ አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከርና ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥር የወል ትርክት ላይ አተኩሮ በመስራት ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በሚከፋፍሉ ትርክቶች ላይ መጠመድ ኢትዮጵያዊነትን እንደማይመጥን ገልጸው፤  በመመካከር እና በመግባባት የሃገርን ከፍታ ማረጋገጥና በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጎልቶ መታየት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡


 

የጋራ ምክር ቤቱ አባል መምህር አለማየሁ መኮንን በበኩላቸው፤  ከፋፋይ ትርክቶች እርስ በእርስ እንዳንተማመንና በጥርጣሬ እንድንተያይ አድርገውን ቆይቷል ብለዋል።

የትርክት መዛባት ቅራኔና አለመግባባቶችን እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የወል  ትርክቶች ላይ በማተኮር ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር መስራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም