በመዲናዋ ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ውጤት ማስገኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አባላቱ ከስልጠናው በተጓዳኝ ትናንት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን የተሞክሮና ልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት፣ የቤት ልማት እና አቅርቦት ስራዎችን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በመዲናዋ ህዝብን በማሳተፍ የተከናወኑ የልማት ተግባራት ውጤት አምጥተዋል፡፡
በቤት ልማትና አቅርቦት ላይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የተከናወኑ ስራዎች አቅርቦቱን ለማሳደግ ማስቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በተሰሩ ስራዎች በርካታ አቅመ ደካሞች ቤት ማግኘታቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በመዲናዋ ህጻናትንና ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች የመፍጠርና መፍጠን መርህን በመከተል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡