የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት ባህር ዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በስድስት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባካሄዳቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አንድ ግብ ተቆጥሮበታል።
ቡድኑ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በስድስት ነጥብ በባህር ዳር ከተማ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ መድን አርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያን በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሽንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ሁለት ግቦችን በጨዋታዎቹ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አንድ ግብ አስተናግዷል።
መድን ሁለት ተስተካካይ ጨዋዎች በአራት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በሁለት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ በአንጻሩ አርባምንጭ ከተማ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ይጫወታሉ።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምድረገነት ሽሬ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ምድረገነት ሽሬ በአምስት ነጥብ 11ኛ፣ ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ጨዋታው ምድረገነት ሽሬ በአራተኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ ካጋጠመው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሲዳማ ቡና ካሸነፈ በሊጉ አራተኛ ድሉን ያስመዘግባል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በስድስት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ሲይዝ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአንድ ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በአራተኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ 2 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በአንጻሩ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታሉ።