ቀጥታ፡

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከማንችስተር ዩናይትድ የሊጉ መሪ አርሰናል ከሰንደርላንድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል። 

በ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። 

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከማንችስተር ዩናይትድ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 በቶተንሃም ሆስፐርስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።


 

ስፐርስ እና ዩናይትድ በተመሳሳይ 17 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ስድስተኛና ስምንተኛ ደረጃን ይዘዋል። 

እ.አ.አ በ2024/25 ቶተንሃም 17ኛ እና ዩናይትድ 15ኛ ደረጃን በመያዝ መጥፎ የውድድር ዓመት ማሳለፋቸው አይዘነጋም።

ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮው የውድድር ዓመት የተሻለ ጅማሮ አድርገዋል። በዛሬውም ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ሰንደርላንድ የሊጉን መሪ አርሰናል በስታዲየም ኦፍ ላይት ያስተናግዳል።


 

አዲስ አዳጊው ሰንደርላንድ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል። በ18 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

በድንቅ ብቃት ላይ የሚገኘው አርሰናል ሊጉን በ25 ነጥብ እየመራ ነው። ካሸነፈ መሪነቱን ያጠናክራል።

መድፈኞቹ አራት የሊግ ጨዋታዎችን ጨምሮ በሁሉም ውድድሮች ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ግብ አላስተናገዱም። 

ለሰባት ዓመት በአርሰናል ለሰባት ዓመታት የተጫወተው እና የቡድኑ አምበል የነበረው የ33 ዓመቱ ግራኒት ሻካ የቀድሞ ቡድኑን በተቃራኒ በመሆን ይገጥማል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች ኤቨርተን ከፉልሃም እና ዌስትሃም ዩናይትድ ከበርንሌይ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ቼልሲ ከዎልቭስ ምሽት 5 ሰዓት በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም