ቀጥታ፡

ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት በቴክኖሎጂ ተደግፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኤጀንሲው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፡- ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ተደግፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክተር አስናቀች ሙህዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተቋሙ የተሟላ ሪፎርም ካደረገባቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የቴክኖሎጂ አሠራርን ማስፋት ነው።

በዚህም መሠረት አገልግሎት የሚሰጠው በሲስተም መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከማዕከል ሆኖ ወረዳ ላይ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን ማየት የሚያስችል ነው ብለዋል።

አሁን አገልግሎት እየሠጡ ካሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የተሻለ እየበለፀገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮች ውጤት እያስገኙ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በቀጣይም እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።

ከብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በ17 ባለሙያ እና አንድ ባለጉዳይ ላይ የተለያየ ርምጃ መወሰዱንና በሕግ ሂደት ላይ የሚገኝ እንዳለም ጠቅሰዋል።

ከ2015 እስከ 2017 በጀት ዓመት በሐሰተኛ መረጃ ለመገልገል በሞከሩ 188 ተገልጋዮችና በአሠራር ጥሰት ደግሞ 589 ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

ብልሹ አሠራርን በመከላከልና መቆጣጠር ሂደት የቴክኖሎጂ ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአብነትም ድርጊቱ በየዓመቱ እየቀነሰ እንዲሄድ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ተገልጋዮች ትክክለኛ መረጃና ማስረጃ አቅርበው አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አስገንዝበው፤ ሕገ ወጥ አሠራር ሲያጋጥማቸው በ7533 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም