ቀጥታ፡

የአፍሪካ ጥያቄ ምጽዋት አይደለም የምንፈልገው የአየር ንብረት ፍትህ እና ፍትሃዊ የፋይናንስ አቅርቦት ነው - መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ምጽዋት አትፈልግም ጥያቄያችን የአየር ንብረት ፍትህ እና ፍትሃዊ የፋይናንስ አቅርቦት ሊኖር ይገባል የሚል ነው ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

ለአየር ንብረት ለውጥ ዝቅተኛ ድርሻ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛውን የጉዳት ቀንበር ሊሸከሙ አይገባምም ብለዋል።

30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 30) ከህዳር 1 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በብራዚል ቤለም ይካሄዳል።

“የአየር ንብረት እርምጃ እና ትግበራ” የጉባኤው ዋና መሪ ሀሳብ ነው።

ከዋናው ጉባኤ በፊት የቤለም የአየር ንብረት የመሪዎች ጉባኤ ተካሂዷል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ወደ ኮፕ 30 ጉባኤ በጠንካራ አቋም መምጣቷን ገልጸው አህጉሪቷ የለውጥ ወኪል ናት ሲሉ ተናግረዋል።

ከፀሐይ ኃይል ማመንጫ ስፍራዎች እስከ አረንጓዴ ኢንቬሽን ባለቤት ወጣቶች የያዘችው አፍሪካ ቀጣዩ ጊዜ ፍትሃዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዝቅተኛ የካርቦን ልህቀት እንዲሆን የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

አፍሪካ የዓለም 40 በመቶ የታዳሽ ኃይል አቅም ያላት ቢሆንም የምታገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ከ12 በመቶ በታች መሆኑን አመልክተዋል።

እኛ የጠየቅነው በጎ አድራጎት አይደለም ያሉት ሊቀ መንበሩ የምንፈልገው የአየር ንብረት ፍትህ፣ ፍትሃዊ የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና እድሎች ተደራሽነት ነው ብለዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ ዝቅተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሀገራት ከፍተኛውን ቀንበር መሸከም የለባቸውም ነው ያሉት።

ኮፕ 30 ዓለም ከቃል መግባት ወደ ለውጥ፣ ከተጋላጭነት ወደ ጥንካሬ መሸጋገር እንዳለበት ገልጸው የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ስራ በአጋርነት፣ በፍትሃዊነት እና የጋራ ብልጽግና እሳቤዎች ሊመራ እንደሚገባውም አመልክተዋል።

ግማሽ መፍትሄ ብቻ የሚያመጡ እርምጃዎችን የመውሰድ ጊዜ አብቅቷል፤ አሁን የሚያስፈልገው ድፍረት የሞላበት እና የጋራ የተግባር ምላሽ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም