ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ስኬቶች ለማስቀጠል የአመለካከትና የተግባር አንድነት መፍጠር ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ):-የብልጽግና ፓርቲ የከፍተኛ አመራር አባላት ሥልጠና እና የመስክ ምልከታ የኢትዮጵያን ስኬቶች ለማስቀጠል የአመለካከትና የተግባር አንድነት መፍጠር የተቻለበት መሆኑን የሥልጠናው ተሳታፊዎች ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራር የአባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና በኢትዮጵያ የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ አመራር አባላቱም ከስልጠናው በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በግብርና መስክ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የልማት ስኬቶችን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በብልጽግና ፓርቲ የከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና የኢትዮጵያን ዕድገት ማረጋገጥ የሚያስችል ግልጸኝነት ተፈጥሯል ብለዋል።


 

ይህም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችንና የዜጎችን ብልጽግና በማስቀጠል የልማት ፍላጎቶችን በጥራትና በፍጥነት መምራት የሚያስችል የዕውቀትና ክህሎት አቅም የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና ተሳታፊዎች የወንድማማችነትና እህትማማችነት አቅሞችን በማጎልበት የተቀናጀ ተግባቦት የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ ምርታማነትና የከተሞች ዕድገት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረቶች ናቸው ብለዋል።

ስልጠናው በብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳታፊዎች መካከልም የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሻሻል የሚያስችል የአመለካከትና የተግባር አንድነት ተግባቦት የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ መልኩም የኢትዮጵያውያንን ሕብረ ብሔራዊ እሴቶች በማጎልበት ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማስቀጠል እንደሚያስችል አንስተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የመስክ ምልከታ የተደረገባቸው የግብርና ዘርፍ ስኬቶችም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ለወጪ ንግድ ጭምር የሚተርፍ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር)፤ በስልጠናው የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያስቀጥል አቅምና ተግባቦት ተፈጥሯል ብለዋል።


 

በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን የቀበሌ አደረጃጀትና የግብርና ምርታማነት ስኬቶችም የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትምህርት የተወሰደባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም በአማራ ክልል የገጠርና ከተማን ትስስር በማጠናከር የገጠር ትራንስፎርሜሽን ስኬቶችን የበለጠ ለማስፋት በተሞክሮ የሚወሰዱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ዑሞድ፤ ለፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት የተሰጠው ስልጠና እና የመስክ ምልከታ ቀጣይ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከፍተኛ ዕውቀትና ክህሎት የተገኘበት ነው ብለዋል።

በስልጠናውም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የልማት ስኬት በማስቀጠል ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ማሻገር የሚያስችል የአመለካከትና የተግባር አንድነት እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች የመስክ ምልከታም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመርቂ ልምድና ተሞክሮ የወሰዱበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም