ቀጥታ፡

ለመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ ታሪካዊ ቀን ነው - ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ለመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ ታሪካዊ ቀን ነው ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ጉብኝት በማድረግ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ገምግመዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በመገጭ የመስኖ ግድብ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ መገጭ ህዝቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታ ሲያቀርብበት የቆየ እና መንግስትም ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2017 ዓ.ም ባሳለፉት ልዩ ውሳኔ አማካኝነት ግንባታውን ይዞ የነበረውን ተቋራጭ በማስወጣት አዲስ ተቋራጭ ገብቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባታው ስራ በባለሙያዎች ተፈትሾ ችግሩን ከምንጩ በመፍታት በፍጥነት እንዲሰራ አቅጣጫ መስጠታቸውን ተናግረዋል።


 

በዚሁ መሰረት ከውጭ አማካሪዎች መጥተው ባደረጉት ጥናት ግንባታው ያጋጠመው የቴክኒክ ችግር ከመሰረቱ እንዲፈታ በማድረግ ፕሮጀክቱ በጤናማ አመራር ስርዓት እየሄደ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።

ግንባታው ከ15 ዓመታት በላይ ላለፈው የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

ውሃው ይፈስበት የነበረውን (ኮርስ) በመቀየር እና በሌላ አቅጣጫ በመውሰድ ግድቡን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመስራት የሚያስችል ተግባር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በተሳካ ሁኔታ መፈጸሙንም ጠቁመዋል።


 

ከዛሬ ጀምሮ ግድቡን ከጫፍ እስከ ጫፍ መስራት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸው ቆሞ የነበረው መዋቅራዊ (ስትራክቸራል) ስራው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

የዋናው ግድብ የአፈር ሙሌት ስራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው አጠቃላይ የግንባታ ስራው ከሰኔ ወር 2018 ዓ.ም በፊት ይመረቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በግንባታው ስራ ላይ እየተሳተፉ ላሉ ተቋራጮች፣ አመራሮች፣ ሰራተኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም