ቀጥታ፡

የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እና ብልፅግናን እውን ለማድረግ ሕዝቡን በማሳተፍ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ):- የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እና ብልፅግናን እውን ለማድረግ ሕዝቡን በማሳተፍ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።      

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአመራር አባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ  እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።  

ከፍተኛ አመራሮቹ ከስልጠናው በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ክላስተር የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።   

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤በጉብኝቱ የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያሳኩ ውጤቶችን አይተናል ብለዋል።  


 

በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በስልጠናውም እነዚህን ውጤቶች በላቀ ደረጃ ማስቀጠል በሚቻልበት አቅጣጫዎች ላይ ተግባብተናል  ነው ያሉት።  

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሕዝቡን በልማት ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮ ሁኔታው እንዲሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።     

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አራት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ ተጨማሪ የኮሪደር ልማት ግንባታዎችን በሌሎች አካባቢዎች ላይ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።  


 

በሁሉም አካባቢዎች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የብልፅግና ፓርቲ ፖሊሲዎችና አቅጣጫዎች ውጤት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ብልፅግናን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ሕዝቡን በማሳተፉ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።      

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤በኦሮሚያ ክልል ያደረግነው ጉብኝት የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።  

ስልጠናውም ተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ እና የጋራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ዕድል የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።  

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንዳሉት፤በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ኢኮኖሚ እድገቱን ለማሳለጥ የሚደረገው ርብርብ ይጠናከራል።  

ለውጡን ተከትሎ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው ውጤቱን ይበልጥ ለማስፋት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።  

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ አርሶ እና አርብቶ አደሩን የግበዓት አቅርቦት ችግር በመፍታት ምርትና ምርታመነት እንዲጨምር በትኩረት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጋራ በማለፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስኬታማ ተግባራትን ለማከናወን በትጋት እንረባረባለን ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም