በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከ1 ሺህ 200 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከ1 ሺህ 200 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ43ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና የሱዳን እና ታንዛንያን ጨምሮ ከ1 ሺህ 200 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ሻምፒዮናው ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውድድሩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በሻምፒዮናው ላይ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ የግል እና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ይሳተፋሉ።
የአትሌቶች ውድድር እድል መፍጠር እና በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም በአሜሪካ ፍሎሪዳ ለሚካሄደው 46ኛው የአለም አገር አቋራጭ ውድድር ሀገር ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን መምረጥ የሻምፒዮናው አላማዎች ናቸው።
በሴቶች በ6 ኪ ሎ ሜትር ወጣት ሴቶች፣ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች እና በ2 ኪሎ ሜትር ውድድሩ ይደረጋል።
8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች እና 2 ኪሎ ሜትር በወንዶች ውድድር የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው።
በሁለቱም ጾታዎች የወጣት ውድድሮች ላይ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
በሻምፒዮናው ላይ በአጠቃላይ 1 ሺህ 209 አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች እንደሚሳተፉ የገለጸው ፌዴሬሽኑ ከሱዳን እና ታንዛንያ በተመሳሳይ አንድ አንድ አትሌቶች እንደሚወዳደሩም አመልክቷል።
ሽልማትን ጨምሮ ለውድድሩ አጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡም በመግለጫው ላይ ተመላክቷል።
ለአሸናፊ አትሌቶች የሚሸለመው ገንዘብ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር እንደሚሸፈን ተገልጿል።