ቀጥታ፡

ብልፅግና በሀሳብ ብቻ ሳይሆን የሚገለጥ ውጤት ማስመዝገቡን በተግባር እያረጋገጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ):- ብልፅግና ፓርቲ በሀሳብ ብቻ ሳይሆን  የሚገለጥ ውጤት ማስመዝገቡን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰሞኑን በአዳማ ከተማ እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።  

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ አመራር አባላቱም ከስልጠናው በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የግብርና ስራዎችን ጎብኝተዋል።   

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ብልፅግና በሀሳብ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ በተጨባጭ የሚገለጥ ውጤት እያሳየ ነው፡፡


 

በኢትዮጵያ ከአሁን በፊት እዚህ ግባ የሚባል የግብርና ሥራ የማይከናወንባቸው የአርሶ አደሩ አካባቢዎች ዛሬ ላይ አስገራሚ ውጤቶች እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ብልፅግና ሲባል ከቤተሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚጀምር መሆኑን ገልጸው፤ ዜጎች የምግብ ሉዓላዊነታቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር ለከተማ ነዋሪዎች ምርት ማቅረብ አስችሏል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የታየው መልካም ጅምር በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ልምድ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አሁን የተጀመሩ ጥረቶች በሁሉም አካባቢ ቀጣይነት ሲኖራቸው የዜጎችን ተጠቃሚነት በተጨባጭ የሚያረጋግጡና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው፤ ስልጠናው በገጠርና ግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በመዋቅራዊ ሽግግር የግብርና ብዝሃ ምርቶችን ማስፋት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል፡፡

በኩታ ገጠም እርሻ፣ ምርጥ ዘር በመጠቀም፣ ገበያ ተኮርና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የግብርና ምርቶችን በማምረት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ፍራፍሬ በኩታ ገጠምና ምርጥ ዘር ተጠቅሞ በማልማት በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆን ጥራት ያለው ምርት በአጭር ጊዜ ማምረት ተችሏል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ያለውን ልምድ በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ምክትል አፈ ጉባኤ አሚና አብዱልከሪም ለኢትዮጵያ ዕድገት የጎላ አበርክቶ ባላቸው የቱሪዝም፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ዘርፎቹ ኢትዮጵያን ወደ መዋቅራዊ ሽግግር የሚመሩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ያላትን አምራች ወጣት፣ ውሃና የመሬት ጸጋ በአግባቡ መጠቅም ያስችላል ብለዋል፡፡

በዚህም በግብርና ምርቶች ላይ ዕሴት በመጨመር፣ ተኪ ምርቶች ላይ በመስራት፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡


 

በብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሻርማርኬ ሙሀሙድ ሀሰን የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናው በተመዘገቡ እመርታዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ለማውጣት የአመራሩን መናበብ በማሳደግ የበለጠ መስራት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት በከተማ ግብርና፣ በሙዝና ፓፓያ ክላስተር እንዲሁም በዓሳ ልማት የመጡ ለውጦች በየአካባቢያችን ያልተጠቀምናቸውን ጸጋዎች ለይተን እንድናለማ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በጋምቤላ ክልል የህግና ፍትህ አካላት ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ኡማን ኦጋላ፤ ስልጠናው ወንድማማችነትን በማጠናከር ሀገራዊ ኃላፊነታችንን በብቃት ለመወጣት ያስችለናል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር እስር በእርስ ለመተዋወቅና ለመተባበር ዕድል እንደሰጣቸው በማንሳት፤ በእስካሁኑ የዜጎችን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በጥራትና በዓይነት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም