ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በኢንተርፕራይዞች ልማት እና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን አጋርነት ፈጠሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በኢንተርፕራይዞች ልማት እና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን አጋርነት ፈጠሩ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር እና የሳዑዲ አረቢያ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባለስልጣን(ሞንሻት) የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።
የሳዑዲ አረቢያ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባለስልጣን(ሞንሻት) ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ፎረም (BIBAN 2025 forum) ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
“የዓለም የእድሎች መዳረሻ” በሪያድ እየተካሄደ የሚገኘው ፎረም ዋና መሪ ሀሳብ ነው።
በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ከሳዑዲ አረቢያ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባለስልጣን(ሞንሻት) ስትራቴጂካዊ አጋርነት መስርቷል።
የአጋርነት ስምምነቱን የተፈራሙት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር እና የሳዑዲ አረቢያ ኢንተርፕራይዝ ባለስልጣን የአጋርነት ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አብዱልሞህሴን ሳሌም አልሳሌም ናቸው።
በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላይ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) እና የሳዑዲ አረቢያ ኢንተርፕራይዝ ባለስልጣን አስተዳዳሪ ሳሚ ኢብራሂም አልሁሴይኒ ተገኝተዋል።
አጋርነቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ስራ ፈጣሪዎች መካከል በኢኖቬሽን፣ በእውቀት ሽግግር እና በገበያ ተደራሽነት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ማጠናከርን ያለመ ነው።
ወጣት መር፣ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ እድገት በማረጋገጥ የቀጣናውን የጋራ ግቦች ለማሳካት እንደሚያግዝም ተመላክቷል።
የሳዑዲ አረቢያ ኢንተርፕራይዝ ባለስልጣን የስራ ፈጣሪዎችን አቅም ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጾ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከርና ሀገሪቱ ለስራ ፈጣሪ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ እድሎችን ለመፍጠር ያላትን ራዕይ ለማሳካት እንደሚሰራ አመልክቷል።
ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ፎረም (BIBAN 2025 forum) ነገ ይጠናቀቃል።