ቀጥታ፡

በሥነ ምግባር የታነፀና ለብሔራዊ ጥቅሞች መከበር  የሚተጋ ትውልድ በመገንባት የድርሻችንን  እንወጣለን-  መምህራን 

ባሕርዳር/  ወልድያ/  ደብረ ብርሃን፤  ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ) ፡-  በሥነ ምግባር  ታንፆ በእውቀት የበቃና ለብሔራዊ ጥቅሞች መከበር  የሚተጋ ትውልድ በመገንባት  ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ  የአማራ ክልል መምህራን ገለጹ። 

"የባዳዎችና የባንዳዎችን ቅዠት በማምከን አንፀባራቂ ድሎችን  እናስመዘግባለን" በሚል መሪ ሃሳብ መምህራን የተሳተፉበት የውይይት መድረኮች ዛሬ በደብረ ብርሃን፣  ባሕርዳር፣ ወልዲያ እና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ተካሂዷል።

ከደብረበርሃኑ መድረክ ተሳታፊዎች ውስጥ  የደብረ ብርሃን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ውሂብ ገብረማሪያም በሰጡት አስተያየት፤  በሥነ ምግባሩ የታነፀ፣ ታታሪና ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመገንባት  በሚደረገው ጥረት የመምህራን ሚና የማይተካ መሆኑን አንስተዋል።


 

መምህርት ዘመት ወልደፃድቅ፤ አሁን ላይ የሰፈነውን ሰላም  ለማፅናትና ለብሔራዊ ጥቅሞች  መከበር  የሚተጋ ትውልድን ለመገንባት  የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።  

የደብረ ብርሃን ትምህርት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ መንግስት ሰላምና ልማት በማረጋገጥ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ  በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል ⵆ

ለአብነትም  በገበያ ማረጋጋት፣ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያኙ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ጠቅሰዋል።

እነዚህን የመሰሉና ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት መምህራን ትውልድን በመቅረጽ ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ በባሕርዳር ከተማ በተካሂደው መድረክ የከተማ አስተዳደሩ  ስራና ክሕሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመነ አሰፋ  እንደገለጹት ፤ መምህራን ሀገር ወዳድና ለብሔራዊ ጥቅሞች መከበር የሚተጋ  ትውልድ መፍጠር አለባቸው።


 

መንግስት ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር የሚያስችል ታላላቅ ፕሮጀክቶችን አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባዳዎችና ባንዳዎች ትስስር በመፍጠር የሀገርን ሰላምና ልማት  ለማደናቀፍ ቢጥሩም በመንግሰትና በሕዝብ ትብብር እየመከነባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወልዲያው የውይይት መድረክ  የከተማው አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት በሪሁን ፤ ከተማዋን  ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።


 

በተመሳሳይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ  ከመምህራን ጋር በአገራዊና ከባቢያዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሄዷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ያምራል ታደሰ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የተረጋጋ አገርን በመገንባት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስቀጠል የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል።


 

በዚህም መምህራን ትውልድን በመገንባት ረገድ ያላቸውን አበርክቶ በማሳደግ ለሀገር ሰላምና ልማት አስተዋፅኦ የሚያበረክት ንቁ ዜጋን ማፍራት ላይ የነበራቸውን ሚና ማጠናከር እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በከተሞቹ በተካሔዱ መድረኮች ላይም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም