በኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ብልፅግናን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ብልፅግናን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ብልፅግናን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአመራር አባላቱን አቅም የሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በሀገሪቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና በከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ከፍተኛ አመራሮችም ከስልጠናው በተጓዳኝ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ብዝሃ ኢኮኖሚ አካሄድን መከተል መጀመራችን ብልፅግናን ለማሳካት ትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ይህም የሚፈለገውን ብልፅግና በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም ገልጸው፤ በግብርናው እና በሌሎችም ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በብልፅግና ሂደት ውስጥ ገጠሩን አካባቢ ማሸጋገርና ማዘመን ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ አርሶ አደሩ ለፍጆታ ከማምረት በዘለለ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በገጠር ትራንስፎርሜሽን እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ከራስ ፍጆታ ባሻገር ለገበያ እስከማቅረብ የዘለቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ገጠሩን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን መመልከታቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ገጠሩን ከከተማው ለማስተሳሰር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በጎ ጅማሮዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ትኩረት በተደረጉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ ኢንዱስትራላይዜሽን፣ የቱሪዝም እምቅ አቅም፣ ከከተማ ልማት ጋር በተያየዙ ብሎም በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ የተደረገው የልማት ስራዎች ጉብኝት መሬት ላይ ተጨባጭ የሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በጉብኝቱ የተመለከቱት የዓሳ ልማት ስራ ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ ብሩህ አዕምሮ እንዲኖራቸውና ምርታማ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዓሣ ልማት ጋር በተገናኘ የተመለከቷቸው ስራዎች የኢትዮጵያ ብልፅግና በአጭር ጊዜ እንደሚረጋገጥ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ያስችላል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡