የጋራ ትርክትን በመገንባት የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማጽናት የድርሻችንን እንወጣለን-የኪነ ጥበብ እና የሚዲያ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ትርክትን በመገንባት የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማጽናት የድርሻችንን እንወጣለን-የኪነ ጥበብ እና የሚዲያ ባለሙያዎች
ደሴ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ):-የጋራ ትርክትን በመገንባት የሀገርን ሰላምና አንድነት ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የድርሻንን እንወጣለን ሲሉ የኪነ ጥበብ እና የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር "ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ከኪነ ጥበብ ፣ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና ከማህበረሰብ አንቂዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሄዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ጋሻው ገብሬ በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የጋራ ትርክት መገንባት ላይ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል።
ለዚህም የኪነ ጥበብ ሙያውን ተጠቅሞ ህብረተሰቡን የሚያስተምሩ በጋራ ትርክት ላይ ያጠነጠኑ ስራዎችን በማቅረብ ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።
የወሎ ባህል ቡድን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሳሙኤል በላይ በበኩሉ፣ የጋራ ትርክትን የሚያጎለብቱና ሰላምን የሚያጸኑ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም በኪነ ጥበብ ስራዎች ባህሎችን በማስተዋወቅ፣ ሰላምን በመስበክ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን በሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አክሏል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዋ እንግዳወርቅ ካሳሁን ፤ጥበብ እያዝናናችና እያዋዛች ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመፍጠር፣ ሰላምን ለማጽናትና የልማት ሥራዎችን ለማጠናከር ያላትን አቅም ተጠቅመን እንሰራለን ብላለች።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትግስት አበበ በበኩላቸው፣ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለሀገር ሰላም፣ ልማትና አንድነት በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።
በዚህም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የመረዳዳት፣ የመጠያየቅና የአብሮነት ልምዶች እንዲጎለብቱ እያደረጉ ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰኢድ ካሳው በበኩላቸው፣ ለከተማዋ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም በየደረጃው ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመው አበረታች ውጤትም እየተመዘገበ እንደሚገኝ አስረድተዋል።