ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል

ጎንደር፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት በ879 ነባርና አዲዲስ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የተፈጥሮ ሀብት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡


 

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ እንደገለጹት፤ ባላፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የልማት ሥራዎች የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል፡፡

ባገገሙ ተፋሰሶች ላይ አርሶ አደሩን በንብ ማነብ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሌሎች የልማት ሥራዎች በማሳተፍ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በቅድመ ዝግጅት ወቅት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ከ473 ሺህ በላይ ተሳታፊ አርሶ አደሮችን በ3ሺህ 66 የልማት ቡድኖች የማደራጀት ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል፡፡

ከ41ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆቱ መሬቶች ላይ የእርከንና ክትር ሥራዎችን ጨምሮ የውሃ ስርገትን የሚጨምሩ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። 

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ የሚከናወንባቸውን ተፋሰሶች በመጪው የክረምት ወራት በስነ ህይወታዊ ዘዴ ለማጠናከርም ከ141 ሚሊዮን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች የማፍላት ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡


 

ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነው የችግኝ ተከላና ክብካቤ ሥራ የዞኑን የደን ሽፋን በአሁኑ ወቅት 14 ነጥብ 5 በመቶ ለማድረስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ አርሶ አደሮች በለሙ አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማግኘታቸው ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ልዩ ትኩረት እየሰጡ መጥተዋል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ክንዱ ዘውዱ ናቸው፡፡


 

በዞኑ የተቋቋሙ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤቶች የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥና ያገገሙ ተፋሰሶች ዘላቂነታቸው እንዲጠበቅ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስረሳው ደሴ በበኩላቸው እንዳሉት ወረዳቸው በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ሞዴል ከሚባሉ ወረዳዎች የሚጠቀስ ነው።

አርሶ አደሮችም በለሙ ተፋሰሶች ላይ በንብ ማነብና በፍራፍሬ ልማት በመሰማራት የተሻለ ገቢ በማግኘት ኑሮዋቸውን እየለወጡ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም