የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ሚናውን ማጠናከር ይጠበቅበታል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ሚናውን ማጠናከር ይጠበቅበታል-ቢሮው
ባሕርዳር፤ ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፡- የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሃሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥ በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት ሚናውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅበት የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለጸ።
የተሳሳቱ መረጃዎችን በመከላከል እና እውነተኛ መረጃን በማጣራት ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ባለሙያዎችን በባሕር ዳር ከተማ ተሰጥቷል።
በስልጠናው መድረክ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ደጀኔ ልመንህ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ ለማሕበረሰቡ በማድረስ ለዘላቂ ሰላም ግንባታው አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ የሆነውን የፅንፈኛውን ቡድን ጥፋት ሕዝቡ እየተረዳ ተግባሩን ማጋለጥና አምርሮም እየተቃወመው መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ችግሩን በመነጋገር በሰለጠነ አግባብ ለመፍታት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉን አስታውሰው፤ በዚህም በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ከተሳሳተ መንገዳቸው በመውጣት መመለሳቸውን አውስተዋል።
ለተመላሾችም የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ መቋቋሚያ ገንዘብና መሰል ድጋፎችን በማድረግ ከማሕበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሕይወታቸውን እየቀየሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
መንግስት አሁንም ለሰላምና ንግግር በሩ ክፍት እንደሆነ አንስተው፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት አፍራሽና ሃሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ሚናውን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሙሉነህ ዘበነ በበኩላቸው፤ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የመንግስትን የሰላም ግንባታና የልማት አጀንዳዎች በጠራ መረጃ ላይ ተመስርቶ በቅንጅትና በትብብር ማድረስ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የክልሉን ዘላቂ ሰላም በመገንባት ሂደት የተዛባና ጥላቻ ተኮር ወሬን በማጋለጥ የላቀ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊና የመድረኩ ጹሑፍ አቅራቢ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ናቸው።
አሁን ላይ ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎች በፍጥነት የመሰራጨት ሰፊ እድል መኖሩን ጠቅሰዋል።
ባለሙያው ተለዋዋጭና ፈጣን ለሆነው የዘመኑን የመረጃ ስርጭት የሚመጥን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በመገንባትም በቴክኖሎጂ ታግዞ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሃሰተኛ መረጃዎችን ማጋለጥ እንዳለበት አመልክተዋል።
በመድረኩ የተቋማት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ሃላፊዎች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎችም አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።