ቀጥታ፡

በቴሌ ብር የሚከናወነው ግብይት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፦በቴሌ ብር የሚከናወነው ግብይት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ቢዝነስ ኦፊሰር ብሩክ አድሃ ገለጹ።

ኢትዮ-ቴሌኮም በግንቦት 2013 ዓ.ም የቴሌ ብር አገልግሎትን በይፋ ማስጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ቢዝነስ ኦፊሰር ብሩክ አድሃና ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግስት የፋይናንስ አካታችነት የሀገሪቷ ስብራት መሆኑን በመለየት አገልግሎቶችን ለማዘመን በትኩረት እየሰራ ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኛን ታሳቢ ያደረጉ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቴሌ ብር ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በቴሌ ብር የሚከናወን ግብይትና የገንዘብ ዝውውር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የቴሌ ብር አገልግሎት የጥሬ ገንዘብ ግብይትን ወደ ዲጂታል የቀየረ መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ ከ56 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች በማፍራት በአራት ዓመት ውስጥ የገንዘብ ዝውውሩ ከአምስት ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በኤሌክትሮኒክ የሚከናወነው ዕለታዊ የገንዘብ ዝውውር በአማካይ 11 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አስታውቀዋል።

ከ800 በላይ ተቋማት አገልግሎታቸውን ከቴሌ ብር ጋር ማስተሳሰራቸውንና ከ300 ሺህ በላይ ነጋዴዎች በቴሌ ብር እየተገበያዩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ቴሌ ብር ገንዘብ የመላክ፣ የተለያዩ ክፍያዎችን የመፈፀምና የብድር አገልግሎት እየተሰጠበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ከ14 ሚሊዮን በላይ ለሚደርሱ ደንበኞች ከ30 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ አነስተኛ ብድር ማቅረብ መቻሉንም አብራርተዋል።

የባንኮችን አገልግሎት በማናበብ የገንዘብ ዝውውርን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም