ቀጥታ፡

ጎንደር ለዓለም አሸብራቂ ከተማ እንድትሆን በትጋት መስራት ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ):- ጎንደር ለዓለም አሸብራቂ ከተማ እንድትሆን በትጋት መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጎንደር ጉብኝት በማድረግ የመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን የሥራ ሁኔታ ገምግመዋል።

በተጨማሪም የፋሲል ግንብ ቤተ መንግስት እድሳት ስራን ተመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፋሲል ግንብ ቤተ መንግስት ለኢትዮጵያ ታላቅ ስጦታ እና የትም የማይገኝ ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህን የመሰለ ስጦታ የሰጡን አባቶቻችን የነሱን ፈለግ ተከትለን ሀገር ብናለማ ሀገር ብንሰራ ዛሬ ኢትዮጵያ ተረጂ አትሆንም ነበር ብለዋል።

የታላቆችን ስራ ማድነቅ፣ ማክበር እና መመርመር መጀመር ለዛ ስራ አንድ ጡብ ወደ ማስቀመጥ እንደሚያሸጋግር አመልክተዋል።

ትናንትናችን ማስታወሻችን መታወሻችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰው ማስታወሻውን መታወሻውን አይዘነጋም አያጠፋም ሲሉ ተናግረዋል።

ኋላውን ማስታወስ የቻለ ሰው እና ማህበረሰብ ዛሬን ለመነሻነት እና ለመስሪያነት እንደሚገለገል ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ የተጀመሩ ስራዎች እና በፋሲል ቤተ መንግስት ግቢ ውስጥ የታየው ለውጥ ልጆቻን ከኛ የተሻለ ተስፋ እንዳላቸው ማሰብ ብቻ ሳይሆን በሚጨበጥ ነገር ለማየት ችያለሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የጎንደር ልጆች አባቶች ያስረከቡትን እና ዛሬ የተሰራውን ስራ የበለጠ በሚያልቅ መልኩ በመስራት የበለጠ ያማረ፣ የተዋበ እና የለማ ሀገር ለመፍጠር የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የፋሲል ቤተ መንግስት መጠገን እና መታደስ ብቻ ዳግም ነው የተወለደው ሲሉም ገልጸዋል።

እንደ ፋሲል ዳግም ውልደት ሁሉ ጎንደር ዳግም እንድትወለድ የሁላችንም መሻት እና ስራ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ከአዘዞ ጀምሮ እስከ ፒያሳ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ጎንደር ዳግም ውልደት መቃረቡን የሚያመለክት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ግብ ለማሳካት የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

ጎንደር ዳግም ተወልዳ ለዓለም አሸብራቂ ከተማ እስክትሆን ድረስ ሁሉም በጋራና በትጋት እንዲሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም