በስፖርቱ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው- ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በስፖርቱ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው- ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፡- አትሌቲክስን ጨምሮ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ አስታወቀ።
ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ በተለያዩ ስፖርት ዘርፎች እየተገኘ ያለው ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም በአትሌቲክስ ዘርፍ በተለይም በሩጫ ከፍተኛ ውጤት ሲገኝ መቆየቱን ጠቅሶ፤ አሁን ግን እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክሱን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርቶች ላይ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠናው አለመመጣጠን ዋነኛ ችግር መሆኑንም አንስቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስፖርቱ በንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ አተኩሮ መመራቱ ለውጤቱ መጥፋት ምክንያት መሆኑን ጠቁሟል ።
የዘርፉ ባለሙያዎች በስፖርቱ ላይ የሚታየውን የአሰራር ችግር በመፈተሽ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት መስራት አለባቸው ሲል አሳስቧል።
በዘርፉ እየጠፋ ያለውን ውጤት ለመመለስ ተግባር ተኮር ስራ ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሞ፤ በተለይ ለስፖርቱ እድገት ጠንካራ የአሰራር ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።
እንደ ሀገር ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከታችኛው እርከን ጀምሮ ጠንካራ የስልጠና፣ የምርጫና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት መስራት ተገቢ መሆኑን ተናግሯል።
ሁሉም አካል በኃላፊነትና በትብብር ከሰራ በሁሉም ስፖርት ዓይነቶች ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ሻለቃ ኃይሌ አስረድቷል።