ቀጥታ፡

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ መሆኑን የሲቪክ ማህበራት ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ (ጂኦግራፊያዊ) እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ የዘገየ መሆኑን በማንሳት፤ጥያቄው ፍትሐዊ፣ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ እና የዜጎችን የመልማት ጥያቄ መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የፍትህ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተፈጥሯዊ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን፤ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል፣ በዲፕሎማሲያዊና በመግባባት መርህ ምላሽ እንዲያገኝ የአካባቢው ሀገራት መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡

ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፥ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጋራ የመልማት የሕዝቦችን ኑሮ የማሻሻልና ቀጣናዊ ትስስር የመፍጠር ዓላማ እንዳለው በማንሳት፤ ሁሉም አካላት በቀናኢነት ሊያዩት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም