አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተመለከትነው ሁሉን አቀፍ ዕድገት እጅግ ተደንቀናል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተመለከትነው ሁሉን አቀፍ ዕድገት እጅግ ተደንቀናል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፡-አዲስ አበባ ከተማ ላይ በተመለከቱት ሁሉን አቀፍ እድገት እጅግ መደነቃቸውን የዓለም የእንስሳት ፕሮግራም ዓመታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
የዓለም የዱር እንስሳት ፕሮግራም አመታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ ከተማን ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ጎብኝተዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ጎብኚዎች መካከል ከኬንያ የመጡት ቪክተር ማሲዚያ፤ አዲስ አበባ በከፍተኛ ለውጥ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፥ እጅግ የተዋበችና ያማረች ሆና ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ከፍተኛ ለውጦች ስለመመዝገባቸው በጉብኝቱ ወቅት መመልከታቸውን ጠቁመው፤ በተለይ በኮሪደር ልማት የተሰሩ ስራዎች የከተማዋን ገጽታ ውብ ማድረግ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነትን አድንቀው ወደ ፊት ደጋግመው ከሚጎበኙት ከተሞች መካከል አንዷና ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛዋ ከቻይና የመጡት ጂዳ ዲ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ በየቀኑ አዳዲስ ለውጦች የሚታዩባት አረንጓዴ ከተማ ለመሆኗ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መናፈሻዎች በስፋት መሰራታቸውን ገልጸው፤ ይህም የአኗኗር ዘይቤን የሚለውጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ አሁን ላይ የአፍሪካ ኩራት የሆነች ከተማ መሆኗን የገለጹት ደግሞ ከአንጎላ የመጡት ሌላኛው ጎብኚ ኖይቲን ቱ ናቸው።
ከካናዳ የመጡት ጎብኚ ጆርጅ ስታድ በበኩላቸው፥ አንድነት ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የከተማዋ ስፍራዎችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ካየዋቸው የዓለም ከተሞች ሁሉ አዲስ አበባን ሁሉም ነገሯ ድንቅና ውብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ነው ያሉት፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ያየሁት እጅግ የተለየ ነው ያሉት ደግሞ ከኢንዶኔዥያ የመጡት ሌሲ ያሰር ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ የቱሪዝም ስፍራዎች መስፋታቸውን ጠቀመው፤ የህዝቡ የኑሮ ዘይቤም የተለወጠበት አስደናቂ ከተማ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
የጉብኝት መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ነው።