ቀጥታ፡

በምእራብ ሸዋ ዞን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

አምቦ ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፡-በምእራብ ሸዋ ዞን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ  ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ በለው ገላሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ የኢቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅና መሰረት ልማትን በማሟላት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጉላት እየተሰራ ነው።

ለዚህም ለሰው ኃይል  ልማትና  የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ  በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢቨስትመንት ዘርፉን ለማበረታታት የሚደረገውን ጥረት በማሳደግም በበጀት ዓመቱ ለ148 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።

የበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ሩብ አመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ለስመዘገቡ 92 አልሚዎች  የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት እነዚህ አልሚዎች ለ1 ሺህ 678 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል። 

ባለሀብቶቹ በዘመናዊ ግብርና እና በአገልግሎት ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ከ464 ሄክታር በላይ መሬት መረከባቸውንም አክለዋል።

አልሚዎቹ  በገቡት ውል መሰረት  ፈጥነው ወደ ተግባር ተሸጋግረው ራሳቸውንና ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም አቶ በለው ገልጸዋል፡፡

በአንጻሩ ለባለሃብቶች ፈቃድ ከመስጠቱ በተጓዳኝ ቀደም ሲል ቦታ ወስደው በአግባቡ ወደ ስራ ያልገቡ 71 ባለሃብቶች  ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በተለያየ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን አክለዋል፡፡

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም