ቀጥታ፡

የጂንካ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባገኘችው የመልማት ዕድል ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች

ጂንካ፤ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ):- የጂንካ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባገኘችው የመልማት ዕድል ፈጣን እድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ውብአለም ገዛኸኝ አመለከቱ።

ከአዲስ አበባ 755 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የጂንካ ከተማ በ1940ዎቹ መጨረሻ እንደተቆረቆረች ይነገራል።

ከተማዋ ባሳለፈቻቸው ዓመታት የመልማት እድል ባለማግኘቷ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ተስኗት ብትቆይም በቅርቡ የተጀመረው የኮሪደርና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች እድገቷን እያፋጠኑ ይገኛሉ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ውብአለም ገዛኸኝ፥ የጂንካ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባገኘችው የመልማት ዕድል ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች።

በከተማው ''ጂንካን በጋራ እናልማ'' በሚል መርህ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የኮሪደርና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመዝናኛ ፓርኮች፣ የአደባባይ ልማት፣ የመንገድ አካፋዮችና ዳርቻዎች የአረንጓዴ ልማት እና የከተማዋን የምሽት ገፅታ የሚያጎሉ የምሽት መብራቶችን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል ።

እያደገ የመጣውን የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት ያማከለ መሰረተ ልማት የመዘርጋቱ ስራ በፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን የጂንካ ንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትም በከተማዋ ከሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ወደ 87 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፥ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን፣ የተቋማትን እና የሆቴሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።

የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንዳሉ ጠቅሰው እነዚህን የልማት ስራዎችን በማፋጠን ጂንካን ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

በከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የመሰረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ ፈለቀ ወርቁ በበኩላቸው የመዝናኛ ፓርኮችን ጨምሮ ህዝባዊ ክብረ በዓላት የሚከናወኑባቸው ውብ፣ ፅዱና ማራኪ ቦታዎችን ያካተተ ስራ በመጀመሪያው ምእራፍ የኮሪደር ልማት መከናወኑን ገልጸዋል ።

በሁለተኛው ምዕራፍ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚተገበርም ተናግረዋል ።

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለማዘመን፣ ዕድገቷን ለማፋጠንና ተወዳዳሪነቷን ለመጨመር ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመው ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ተመራጭነቷን እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል ።

የጂንካ ከተማ በአሪ ዞን እና በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ቱሪስቶች መዳረሻ ስፍራ በመሆን እያገለገለች ያለች የጠረፍ ከተማ ናት።

የጂንካ ሙዚየምን ጨምሮ የከተማዋን ጎዳናዎች፣ የገበያ ስፍራዎችን እና የመዝናኛ ፓርኮችን በመጎብኘት አስደሳች ጊዜ እያሳለፉ እንዳሉ የተናገሩት የቼክ ሪፐብሊክ ዜግነት ያላቸው ጥንዶች ቬሮኒካ ቱች ኮቫ  እና ባትስላቭ ሚልራደር ናቸው።

ወደ ጂንካ ሲመጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው፥ ከ6 ዓመታት በፊት  ከጎበኟት ጂንካ ከተማ በእጅጉ የተለየ ፈጣን ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም