በሐረሪ ክልል በትምህርት ዘመኑ 40 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መረሀ ግብር ተጠቃሚ ይሆናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል በትምህርት ዘመኑ 40 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መረሀ ግብር ተጠቃሚ ይሆናሉ
ሐረር፤ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በትምህርት ዘመኑ 40ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መረሀ ግብር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ከእነዚህ ተግባራት መካከል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፤የትምህርት ግብዓት ማሟላት፤ የተማሪዎች ምገባ፤ የመምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
የሐረሪ ክልላዊ መንግስትም በወሰዳቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በትምህርት ዘርፉ የተሻሉ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘከሪያ አብዱልአዚዝ ለኢዜአ እንዳሉት፥ ክልሉ በትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልና በግብዓት ማሟላት ረገድ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎን የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርንም በገጠር እና በከተማ በሚገኙ 67 ቅድመ መደበኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የተመጣጠነ ምግብን በማቅረብ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ የሚሆኑበትንና ማርፈድና መጠነ ማቋረጥን በእጅጉ እየቀነሰ ነው ብለዋል።
ተግባሩ የመማር ማስተማር ስራዎችን በማቀላጠፍ የተማሪዎች ውጤትን በማሻሻሉ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት ማገዙን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስት ለተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር አስፈላጊውን በጀት መመደቡን አንስተው፥በዚህም ከቅድመ መደበኛ እስከ አንደኛ ደረጃ ያሉ 40 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።
ለመጋቢ እናቶች ስልጠና የመስጠት እና ሌሎች አስፈላጊ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።