ቀጥታ፡

የክልሎችን መልከዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የሆርቲካልቸር ፓርኮች ይገነባሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፡-የክልሎችን መልከዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የሆርቲካልቸር ፓርኮች እንደሚገነቡ በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አብደላ ነጋሽ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ አካባቢ ያለውን የግብርና ሁኔታ በተመለከቱበት ወቅት የሆርቲካልቸር ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሮች የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትንና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በስፋት መጠቀም መቻላቸው በአንድ ሄክታር የሚገኘው ምርት እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል፡፡

እንዲሁም በክላስተር የሚከናወነው የግብርና ስራ የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የፓፓያ፣ የአቦካዶና የሙዝ ምርቶችን በምርምር በማሳደግ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል መመልከታቸውን ነው የገለጹት።

ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት በእጅጉ እንደሚያግዝ በመስክ ጉብኝቱ ላይ ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አብደላ ነጋሽ እንደገለጹት፤ የሆርቲካልቸር ዘርፉን በሚፈለገው ልክ ለማልማት እየተሰራ ነው።

በዚህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግና ዘርፉን በተሻለ መልኩ የሚለውጥ ሀገራዊ ስትራቴጂ ስራ ላይ መዋሉንም አስታውቀዋል።

ስትራቴጂው በሆርቲካልቸር ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ስትራቴጂው የሆርቲካልቸር ፓርኮችን መመስረት ታሳቢ ማድረጉን ጠቅሰው፥ይህም በተለይ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ስትራቴጂው በዘርፉ ያለውን ማነቆ በመፍታት በመስኩ የሚፈሰውን መዋዕለ ንዋይ ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ በተያዘው ግብ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ 10 ቦታዎች ላይ የሆርቲካልቸር ፓርኮች እንደሚገነቡ ነው የተናገሩት።

ግንባታ የተጀመረባቸው ክልሎች መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም