ባለሃብቶች የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚያረጋግጡ ዘርፎች ላይ ይበልጥ ማተኮር ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለሃብቶች የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚያረጋግጡ ዘርፎች ላይ ይበልጥ ማተኮር ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 28/2018(ኢዜአ)፡-ባለሃብቶች የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚያረጋግጡ ዘርፎች ላይ ይበልጥ ማተኮር እንደሚገባቸው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውን ገልጸዋል።
በሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት ሀገርን ከጸጋዎቿ በማሰናሰል በብዝኀ የኢኮኖሚ ልማት ዕመርታዊ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋታቸውንም ተናግረዋል።
ይህ ማሻሻያ ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሚያስችላትም አስረድተዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን እንዳሉት፤ የማፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ለሀብት ፈጠራ፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ ትልቅ ሚናን ይጫወታል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪው ከራሱ አልፎ ሌሎች ዘርፎች እንዲነቃቁ መሠረት የሚጥል መሆኑን ጠቅሰው፤ የአገልግሎት፣የትራንስፖርትን ጨምሮ ለንግድ ዘርፉም መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ካለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያበረክተው ታላቅ ሚና አንጻር ነው ብለዋል፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪ፣ ከተማና መሠረተ ልማት እና ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል አስተባባሪ መሪ ተመራማሪ አማረ ማተቡ (ዶ/ር)፤ አምራች ኢንዱስትሪው ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን አንስተዋል፡፡
በሌላ መልኩም አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያለውን በጎ ሚና ጠቅሰው፤ የወጭ ንግድን ለማሳደግ እንዲሁም ተኪ ምርቶችን በብዛትና ጥራት ለማምረት ያለውን በጎ ሚናም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የወጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ተኪ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችንም መደገፍና ማበረታታ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪውን በተመለከተ መንግስት ግልጽ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ጠቁመው፤ ይህን የሚያስፈጽሙ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ባለሃብቶችም መንግስት የዘረጋውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና በሚያመጡ ዘርፎች ላይ መሰማራት የበለጠ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመሩ ስራዎችን ውጤታማነትንም ጠቁመዋል፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪና የማዕድን ዲፓርትመንት ኃላፊና መሪ ተመራማሪ ነጻነት ጆቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪው ዕድገት የመንግሥት የፖሊሲ ውጤት መሆኑንም ጠቁመው፤ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ የመንግሥት ቀጣይ ትኩረት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።