የአዳማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ ለመዝናናት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ ለመዝናናት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዳማ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፡-የአዳማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ ለመዝናናት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ።
በአዳማ ከተማ በኮሪደር ልማት ስራ አረንጓዴና የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ፣ የህፃናትና ታዳጊዎች መጫወቻ፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ያካተተ ነው።
ነዋሪዎቹ የኮሪደር ልማቱ ልጆችና ታዳጊዎች የሚጫወቱበትና የሚቦርቁበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ መጪው ትውልድ የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።
በአዳማ ከተማ ወንጂ ማዞሪያ አካባቢ በሚገኝ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ ከአራት ልጆቻቸው ጋር ሲዝናኑ ያገኘናቸው ወይዘሮ መቅደላዊት ደጀኔ በሰጡት አስተያየት በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት አዳማን ከተጨናነቀና ንፁህ ካልሆነ ከባቢ በማላቀቅ ተስማሚና ውብ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል።
በተለይ ከልጆቻቸው ጋር ለመዝናናት የመጡበት ይህ የህዝብ ፓርክ በፊት የቆሻሻ መጣያ እንደነበር አስታውሰው አሁን ገጽታው ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛ ስፍራ ሆኖ ስላገኙት መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ለተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ ምቾት የማይሰጡና ለአደጋ ሲያጋልጡ የነበሩ የከተማዋ ጠባብ መንገዶች ደረጃቸውን በሚመጥን መልኩ ሰፋ ብለው መሰራታቸው፣ የአረንጓዴ ፓርክ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ ማካተታቸው ደግሞ በቀንም ሆነ በምሽት ከቤተሰብ ጋር የእግር ጉዞ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልናል ብለዋል።
አቶ መሀመድ አማን፤ የኮሪደር ልማት ስራው ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ የመዝናኛ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ ታዳጊ ህፃናትን ጨምሮ ለእንቅስቃሴና መዝናኛ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረውን የከተማውን እድገትና ደረጃ ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኮሪደር ስራው የታክሲና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ከመለየት ባለፈ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዱም ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ወጣት ሮዛ ነጌሶ በበኩሏ በኮሪደር ልማት ምክንያት መንገድ በመዋቡ ለንግድ ስራም ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጻለች።
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ንፅህናና ውበት ከማስጠበቅ ባለፈ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ የሕዝብ መዝናኛዎችና ማረፊያዎችን በመፍጠሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረጉ ልማቱን ልንጠብቅና ልንንከባከበው ይገባል ብላለች።
በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ ከተማውን ውብ እና ለነዋሪዎቿና ለቱሪስቶች ምቹ እንዲሁም ተመራጭ የሚያደርጋት መሆኑንም አንስታለች።
በአዳማ የኮሪደር ልማትን ተከትሎ ዘመናዊና አዳዲስ የመንገድ መብራቶች መተከላቸው አካባቢውን ልዩ ገፅታ በማላበስ ከተማዋን ውብና ለኑሮ ተስማሚ እያደረገ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አሸብር ኃይለማርያም ናቸው።
በተለይ እርሳቸው የእለት ስራቸውን በሚያከናውኑበት አካባቢ በኮሪደር ልማቱ በሁለቱም የመንገድ ዳርቻዎች ለእግረኛ ምቹ መንገዶች መገንባታቸው አካባቢውን ውብ ገፅታ ከማላበስ ባለፈ የስራ አካባቢያቸውን እንዲወዱና ስራቸውን በትጋት ለመስራት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።