በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት ለማህበረሰቡ የተሻለና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት ለማህበረሰቡ የተሻለና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እያገዘ ነው
ቦንጋ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጤና መድህን አገልግሎት ለማህበረሰቡ የተሻለና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እያገዘ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች በበኩላቸው የሚያገኙት አገልግሎት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሒም ተማም ለኢዜአ እንደገለጹት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በማሳደግ የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በ2017 ዓ.ም በክልሉ 421ሺህ 541 እማውራና አባውራዎችን የጤና መድህን አባል ተጠቃሚ በማድረግ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋንን ከ75 ነጥብ 6 በመቶ ላይ ለማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚሁ በጀት ዓመት ከአባላቱ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰ መቻሉን ጠቁመው፣ የአባላትን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሻሻል በተሰራው ሥራ ውጤት እየታየ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለዚህም ቀደም ሲል ከመድሀኒት እጥረት ጋር በተያያዘ ይነሳ የነበረ ችግር እየተፈታ መምጣቱንና በአገልግሎቱ ላይ የደንበኞች የእርካታ ማነስ መሻሻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል አዳዲስ አባላትን ለማፍራት፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት ጥራትን ለማሳደግና የመድሀኒት አቅርቦት ችግርን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
እንደ አቶ ኢብራሒም ገለጻ አገልግሎቱን ለማሻሻል በመጀመሪያ ሩብ ዓመቱ ከ139 ሚሊዮን 544 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በክልሉ ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተሰጥቷል።
ይህም በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የበጀት ችግር በማቃለል በተለይ የመደሀኒት አቅርቦቱ እንዲሻሻል ጉልህ አስተዋጾ ማድረጉን ነው የገለጹት።
በዋቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለሕክምና የመጡት የጤና መድህን አባላት በበኩላቸው የጤና እክል ሲገጥማቸው ያለችግር መታከም እንደቻሉ ተናግረዋል።
በአባልነታቸው በዓመት አንዴ የከፈሉት መዋጮ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ከተጠቃሚዎች መካከል ከቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ ለተሻለ ሕክምና ባለቤታቸውን በሪፈር ይዘው እንደመጡ የገለፁት ወይዘሮ ጀሚላ ሻፊ፣ ወደሆስፒታሉ ከመጡ አራት ወር እንደሆናቸው ገልፀዋል።
በሆስፒታሉ ቆይታቸው ያለተጨማሪ ወጪ ባለቤታቸውን እያሳከሙ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በሆስፒታሉ ከመድሀኒት አቅርቦት፣ ከመስተንግዶና ከላቦራቶሪ አገልግሎት ጋር መሻሻል ታይቷል ብለዋል።
በጨና ወረዳ ቦባጎታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ አበቶ በበኩላቸው የጤና መድህን አባል ከመሆናቸው በፊት የጤና እክል ሲገጥማቸው በገንዘብ እጦት ምክንያት ፈጥነው ወደ ጤና ተቋማት እንደማይሄዱ አስታውሰዋል።
የጤና መድህን አባል ከሆኑ ወዲህ ሲታመሙ ፈጥነው ወደ ሕክምና ስለሚሄዱ የሳቸውና የቤተሰቦቻቸው ጤና ሁኔታ በእጅጉ መሻሻሉን ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም የወባ በሽታን ጨምሮ የሚታዘዙ ሌሎች መደሀኒቶች በበቂ ሁኔታ ስለማይገኝ ለከፍተኛ ወጪ እንዳረግ ነበር ያሉት ነዋሪው፣ አሁን ይህ ችግሩ እየተፈታ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በዋቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ሙሉዓለም በላይ (ዶ/ር) ናቸው።
በተለይም የማህበረሰብ ሞዴል ፋርማሲ ከተከፈተ ወዲህ በመድሀኒት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ነው የተናገሩት።