የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከነገሌ አርሲ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችንም ሲያስቆጥር አንድ ጎል አስተናግዷል።
ቡድኑ በ10 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
አዲስ አዳጊው አርሲ ነጌሌ በውድድር ዓመቱ ባከናወናቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አራት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በሁለት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ጨዋታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድል ጉዞው ለመቀጠል ነጌሌ አርሲ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።
በሌላኛው መርሃ ግብር ወላይታ ድቻ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 10 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።
ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ባካሄዳቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በአንድ ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ጨዋታው ቡድኖቹ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
መቻል ሊጉን በ10 ነጥብ እየመራ ይገኛል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የሃዋሳ ከተማ ተጫዋቾቹ ጌታነህ ከበደ እና ያሬድ ብሩክ፣ የፋሲል ከነማው በረከት ግዛው እና የመቻሉ መሐመድ አበራ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር በጋራ ይመራሉ።