የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። ቡድኑ በሶስት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ ከአራት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዷል። ሃዋሳ ከተማ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አዲስ አበባ ከተማ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በሶስት ነጥብ 12ኛ፣ ሸገር ከተማ በስድስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የዕለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር ልደታ ክፍለ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ያገናኛል።
ልደታ ክፍለ ከተማ በአምስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ ሊጉን ይመራል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በስምንት ግቦች ትመራለች።
የልደታ ክፍለ ከተማዎቹ ቃልኪዳን ጥላሁንና ረድኤት ዳንኤል፣ ቱሪስት ለማ፣ ቤተልሄም መንተሎ እና ትዕግስት ወርቁ ከመቻል፣ ምትኬ ብርሃኑ ከሲዳማ ቡና፣ ፊርማዬ ከበደ ከድሬዳዋ ከተማ እና የሸገር ከተማዋ ሰናይት ኡራጎ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ።