ለጆሮ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? - ኢዜአ አማርኛ
ለጆሮ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንገት በላይ ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም ኦሊያድ ታረቀኝ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ስለ ጆሮ ህመም መንስዔ እና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ አብራርተዋል።
የጆሮ ህመም ምንድን ነው?
እንደ ዶክተር ኦሊያድ ገለጻ፤ በጆሮ አካባቢ ያሉ የአካል ክፍሎችን የሚያጠቁ ህመሞች የጆሮ ህመም ሊባሉ ይችላሉ።
በሳይንሱ የውጨኛው፣ የመካከለኛው እና የውስጠኛው የጆሮ ክፍል ህመም ተብለው እንደሚለዩ ጠቅሰው፤ እነዚህን ክፍሎች የሚያጠቁ የተለያዩ የህመም ዓይነቶች እንዳሉም አመላክተዋል።
የጆሮ ህመም ዓይነቶች
በተለያዩ መንስዔዎች የተለያዩ ህመሞች እንደሚከሰቱ ጠቁመው፤ ከእነዚህ መካከል በስፋት የሚከሰተው በኤንፌክሽን የሚከሰት የጆሮ ህመም መሆኑን ተናግረዋል።
ከአደጋዎች፣ ህመሞችና ጉዳቶች ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የጆሮ ክፍሎች ህመሞች እንዳሉም በመጠቆም።
እንዲሁም ከዕባጮች (ዕጢዎች) ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጆሮ ህመሞች እንዳሉ አመላክተዋል።
በውጨኛው የጆሮ ክፍል የሚከሰቱ ከአጥንትና ከቆዳ የሚነሱ ዕባጭና ዕጢዎች፣ ከመካከለኛው የጆሮ ክፍል የሚነሱ በአብዛኛው ከደም ሥር ጋር የተያያዙ ዕጢዎች እንዲሁም ከውስጠኛው የጆሮ ክፍል ከነርቭ የሚነሱ የተለያዩ ዓይነት ዕጢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አብራርተዋል።
ለጆሮ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች
የጆሮ ህመም በሁሉም ጾታና የዕድሜ ክልል ሊከሰት እንደሚችል ገልጸው፤ በአብዛኛው አጋላጭ ምክንያቶች ተብለው ከሚነሱት መንስዔዎች መካከል ከታች የተጠቀሱት ዋነኞቹ መሆናቸውን ያብራራሉ።
o ባብዛኛው ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች (ልጆች ባላቸው ያልዳበረ በሽታዎችን የመከላከል ዐቅም እንዲሁም አንዳንድ የሰውነት ክፍሎቻቸው በደንብ ባለመዳበራቸው ሊከሰት የሚችል ነው።)
o ዕድሜ ሲጨምር የጆሮ መዳከም ችግር ሊኖር ስለሚችል የመስማት ዐቅም እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል።
o ለተለያየ ከባድ ድምጽ መጋለጥ ለጆሮ ህመም ወይም የተለያየ ደረጃ ላላቸው የመስማት ችግሮች ሊዳርግ ይችላል።
o ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት ጭሶች መጋለጥ ለጆሮ ህመም ሊያጋልጥ ይችላል ተብሎ እንደሚታሰብ አስረድተዋል።
የጆሮ ህመም ምልክቶች
ምልክቶቹ እንደ ህመሙና ህመሙ እንደተከሰተበት ቦታ የተለያዩ መሆናቸውን ዶክተር ኦሊያድ ይገልጻሉ።
ለምሳሌ በኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰት የጆሮ ህመም ከሆነ እንደተከሰተበት የጆሮ ክፍል ምልክቱ ይለያያል ይላሉ። ለአብነትም የውጨኛው የጆሮ ክፍል ላይ የሚከሰት የጆሮ ኢንፌክሽን ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል መጠዝጠዝ፣ ውጋትና ማሳከክ ዋናኞቹ ናቸው ብለዋል።
ራሱ ይህ ህመም በመካከለኛው የጆሮ ክፍል ላይ ሲከሰት ደግሞ የመስማት ደረጃ መቀነስ፣ ትኩሳት፣ አልፎ አልፎ ከባድ የጆሮ ውጋት መኖር፣ የህመሙ ደረጃ እየጨመረ ሲሄድም የተለያዩ ፈሳሾችን ሊያሳይ ይችላል (ለምሳሌ እንደ ውኃ የቀጠነ ፈሳሽ፣ ወፍራም መግል የመሰለ ፈሳሽ፣ አንዳንድ ጊዜ ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ሊሆን ይችላል ሲሉ አብራርተዋል።)
በተለያዩ ዕባጮችና ዕጢዎች የሚከሰት የጆሮ ህመም ሲሆን ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፤ የጆሮ መደፈን ስሜት (ጆሮ ድፍን ብሎ ለመስማት መቸገር)፣ የተለያየ ዓይነት የጆሮ ውስጥ ድምጽና ጩኸቶች መኖር (አንዳንድ ጊዜ ከልብ ምት ጋር አብሮ ሊሰማ የሚችል የጆሮ ውስጥ ጩኸት ሊሆን ይችላል) ብለዋል።
በውስጠኛው የጆሮ ክፍል ላይ የሚከሰት የዕጢ ዓይነት ደግሞ የመስማት ደረጃ መቀነስ፣ ማዞር እና ቫላንስ እስከ ማጣት (ሚዛንን ጠብቆ ለመንቀሳቀስ እስከመቸገር) የሚያደርሱ ምልክቶችን ሊያሳይ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ሰዎች ለጆሮ ህመም እንዳይጋለጡ ምን ያድርጉ?
ሰዎች የተለያዩ ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መክረው፤ ከእነዚህ ጥንቃቄዎች መካከልም፡-
o በልማድ የሚደረጉ ጭራሽ ለጉዳት አጋላጭ የሆኑ ጆሮን የማጽዳት ተግባራት (‘የጆሮን ንጽህና እየጠበቅሁ ነው’ ብሎ በማሰብ ጆሮን ለማጽዳት የሚደረጉ ልማዶችን) ማስወገድ፤
o ጆሮ ለከባድ ድምጽ እንዳይጋለጥ ማድረግ። ለምሳሌ ለረጅም ሠዓት ‘ኤርፎን’ መጠቀም ለጆሮ ህመም እንደሚያጋልጥ በመገንዘብ የሠዓቱን እና የድምጹን መጠን መቀነስ እንደሚገባ መክረዋል።
‘ኤርፎን’ በአንድ ጊዜ ለ60 ደቂቃ የድምጽ መጠኑ ከ60 በመቶ ባልበለጠ ጊዜ መጠቀም ይመከራል ያሉት ዶክተር ኦሊያድ፤ ከዚህ ደቂቃ በላይ በአንድ ጊዜ መጠቀም ሲያስፈልግ በየመሀሉ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ጆሮን ማሳረፍ እንደሚገባ ይመክራሉ።
በሌላ በኩል ማሳከክን ጨምሮ የጆሮ ህመም ስሜት ሲኖር በወቅቱ ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታ በማድረግ ህመሙ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ መታከም የጥንቃቄው አካል መሆኑን አስረድተዋል።
የጆሮ ህመም ሕክምና
ሕክምናው እንደ ህመሙ ዓይነት እንደሚለያይ አስገንዝበው፤ በአጠቃላይ በሚዋጡ፣ በመርፌ በሚሰጡ፣ በጆሮ ውስጥ በሚጨመሩ እንዲሁም በሚቀቡ አማራጮች ሕክምናው እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
ከላይ ከተጠቀሱት የሕክምና አማራጮች አልፎ የመስማት ደረጃ መቀነስና መቸገር ከተስተዋለ የቀዶ ሕክምና ማድረግ ብሎም የማዳመጫ ማገዣ መሣሪያ መጠቀም የሕክምናው አካል መሆናቸውን አስረድተዋል።
የጆሮ ህመም በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ከ5 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ልጆች ላይ 8 በመቶ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ60 በላይ በሆኑ ሰዎች ደግሞ እስከ 73 በመቶ ድረስ የመስማት ችግር እንደሚያጋጥም ጥናት ማመላከቱን ጠቅሰዋል።
ጆሮ ላይ የሚከሰቱ ህመሞች የመስማት ችግርን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።