የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህዳር ወር በአንጎላ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህዳር ወር በአንጎላ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፡- ሰባተኛው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ህዳር 15 እና 16 ቀን 2018 ዓ.ም በአንጎላ ሉዋንዳ ይደረጋል።
ጉባኤውን የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጆአኦ ሎሬንቾና የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት አንቶኒዮ ኮስታ በጋራ ይመሩታል።
የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች፣ የህብረቱ ሀገራት መሪዎች፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የንግድ ልዑካን በጉባኤው ይሳተፋሉ።
የሁለቱ ተቋማት አጋርነት 25 ዓመታትን ባስቆጠረበት ወቅት የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ኢ-ተገማችነት እያደገ በመጣበት ዓለም እና የጂኦ ፖለቲካ ምህዳሮች እየተቀየሩ ባሉበት ጊዜ የሚከናወን መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
የተቋማቱ መሪዎች ለባለብዙ ወገን ትብብር፣ አጋርነት እና እየታዩ ላሉ ፈተናዎች የተቀናጀ ምላሽ የመስጠት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን እንደሚገልጹ አስታውቋል።
ሰላም፣ ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት፣ ፍልሰት እና የሰዎች እንቅስቃሴና የሰው ኃይል ልማት ውይይት ከሚደረጉባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የሚወያዩባቸው ጉዳዮች በአጀንዳ 2063፣ በዘላቂ የልማት ግቦችና የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የ2030 የጋራ ራዕይ ጋር የተቆራኙ መሆናቸው ተመላክቷል።
ከዋናው የመሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ የወጣቶች እና የሲቪክ እንዲሁም የንግድ ፎረሞች ይካሄዳሉ።
በፎረሞቹ ላይ ወጣት መሪዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የሚያነሷቸው ሀሳቦች በመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚቀርቡ ህብረቱ ገልጿል።
ስድስተኛው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እ.አ.አ በ2022 በቤልጂየም መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ በነበረው ጉባኤ የሁለቱ ተቋማት አባል ሀገራት የ2030 የጋራ ራዕይ ማዕቀፍ ያፀደቁ ሲሆን 150 ቢሊዮን ዩሮ ገደማ የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ይፋ ሆኗል።
የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት አጋርነት በይፋ የተጀመረው እ.አ.አ በ2000 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።