ቀጥታ፡

የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር የአህጉሪቱን ዕድገት በማሳለጥ ለዜጎች ተጠቃሚነት መሠረት እየጣለ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር የአህጉሪቱን ዕድገት በማሳለጥ ለዜጎች ተጠቃሚነት መሠረት እየጣለ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ገለጸ።

''ቻይና ለአፍሪካ ኢንዱስትሪ፣ ለአረንጓዴና ዘላቂ ልማት ድጋፍ ታደርጋለች’’ በሚል መሪ ሀሳብ በቻይና የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ፣ የውይይት የጥናትና ትብብር ማዕከል እና በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (POA) ትብብር የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የፋይናንስና አስተዳደር ዳይሬክተር ስቴቨን ካሪንጊ(ዶ/ር)፤ ቻይና ለአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ድጋፍ እያደረገች ነው ብለዋል።

የቻይና አፍሪካ የኢንዱስትሪና ዲጂታላይዜሽን ልማት ትብብር ለአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት መሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቀጣይም የአፍሪካን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ ቻይና በኃይል አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታና በሰው ሃብት ልማት የምታደርገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በቻይና አፍሪካ ልማት ፈንድ የኢትዮጵያ ቢሮ ተወካይ ሊ ሺባኦ፤ ቻይና ስትራቴጂክ የልማት አጋርነት ዕቅድ በመቅረጽ ለአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረገች ነው ብለዋል።


 

በዚህም የቻይና ባለሃብቶች የአህጉሪቱን ዘላቂ ዕድገት የሚያሳልጥ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ በማድረግ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በቻይና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሊዩ ዩኢ፤ የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር በስኬታማ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።


 

የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ሥነ-ምኅዳር ግንባታ ትብብርም በሁሉም የኢኮኖሚ መስክ የአህጉሪቱን ዕድገት ለማስቀጠል መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የቻይና የሥራ ኃላፊዎች የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የዘርፍ ኮሚሽነሮችና የተጋባዥ ተቋማት እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም