ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትህ አካላት በቅንጅት መስራታቸው በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትህ አካላት በላቀ ቅንጅት መስራታቸው  በዘርፉ  መሰረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን  የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት  ዓለምአንተ አግደው አስታወቁ። 

የክልሉ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የትብብር መድረክ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የ2018 በጀት ዓመት ሶስት ወራት  ዕቅድ አፈጻጸም በባሕርዳር ከተማ እየገመገመ ነው።


 

በግምገማው መድረክ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት፤ የዳኝነትና የፍትህ አካላት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተቀናጅተው በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።

የተቋማቱ ቅንጅትም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያና ፍትህ ቢሮ  ያካተተ መሆኑን  ተናግረዋል።

ተቋማቱ ነጻነትና ገለልተኝነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ስራቸውን በተቀናጀ ትብብር በመስራታቸው የክልሉን የፍትህ ስርዓት ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ   መቻሉን  አስረድተዋል።

በዚህም በዳኝነትና ፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በትብብር በመሙላትና ጥንካሬዎቻቸውን በማስቀጠል  መሰረታዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማዘመን ይበልጥ  ተደራሽ ለማድረግም  የሰው ሃብት አቅም መገንባት ላይ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

ይህም ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ለወጭና እንግልት ሳይዳረጉ የርቀት ክርክሮችንና ቅሬታ የሚያቀርቡበት ስርዓት መዘርጋት እንዳስቻለም  አንስተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር  ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው፤  የፍትህና ዳኝነት አካላት በቅንጅትና ትብብር መስራታቸው  ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ማረሚያ ቤቶች የፍርድ ውሳኔ ያገኙ ዜጎችን በአግባቡ በማረምና  በመልካም ስነ ምግባር የማነፅ ተግባር ላይ  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ የክልሉ  ማረሚያ ቤቶች  ኮሚሽነር  ሃብታሙ ሲሳይ ናቸው።  

ተቋማቱ በቅንጅትና ትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል ህጋዊ ማዕቀፍ ያለው አሰራር መዘርጋቱ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀን በሚቆየው መድረክ የክልሉ የዳኝነትና ፍትህ ተቋማት አመራሮች በመሳተፍ ላይ  ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም