በደብረ ብርሃን ከተማ 85 ሺህ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሃን ከተማ 85 ሺህ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ ነው
ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 27/ 2018 (ኢዜአ) ፡- በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር 85 ሺህ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጋ ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ወጣትና ስፖርት መምሪያ ገለጸ።
በከተማው እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ ቀደም ሲል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ 16 የመኖሪያ ቤቶች ዛሬ ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።
በዘህ ወቅት በመምሪያው የወጣቶች አደረጃጀት ማካተትና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ አወቀ ሀይለማሪያም እንዳመለከቱት፤ በከተማው እየተከናወነ ያለው የበጋ ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እየተከናወነ ነው።
በበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የደም ልገሳ፣ 117 አዲስ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባትና ያረጁ ቤቶችን የመጠገን ስራን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት እንደሚከናወኑ አንስተዋል።
በዚህም 85 ሺህ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ በለጥሽ ግርማ በበኩላቸው፤ በበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሴቶችና አረጋውያን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዛሬ ለተጠቃሚዎች የተላለፉት 16 የመኖሪያ ቤቶች የዚሁ አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ በሀይሉ ገብረህይወት እንዳሉት ፤ አስተዳደሩ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በራስ አቅም በመርዳት ችግራቸወን መፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተንከባካቢና ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች በማገዝ የተጀመረው አገልግሎት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የመኖሪያ ቤት እድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።