ቀጥታ፡

የወረዳው አርሶ አደሮች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተሰማርተዋል

ሮቤ ፤ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፡-በአካባቢያቸው የሚገኙ  የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የበጋ መስኖ  ስንዴን እያለሙ መሆናቸውን የባሌ ዞን ጋሠራ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። 

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ከ183 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ 

ከጋሠራ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሼህ አህመድ ከድር በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የወንዝ ውሃን በሞተር ፓምፕ በመሳብ ባለፉት ሦስት ዓመታት  ስንዴንና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬ በማፈራረቅ  በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው ።

ዘንድሮም  አንድ ሄክታር መሬታቸውን  በበጋ መስኖ  ስንዴ ለማልማት ወደ ስራ መግባታቸውንና  ከዚህም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ  ገልጸዋል። 

ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅትን  ብቻ በመጠበቅ ከሚያለሙት ሰብል የእለት ፍጆታቸውን መሸፈን እንዳልቻሉ ያስታወሱት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ከማል አብዱ ናቸው። 

ባለፉት አመታት  በተሰማሩበት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመሰማራታቸው  ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው  ማደጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው የሚገኘውን ወንዝ በሞተር ፓምፕ በመሳብ ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በኩታገጠም አሰራር ስንዴንና ሌሎች ገቢ የሚያስገኙ ሰብሎችን እያለሙ መሆናቸውን አመልክተዋል። 


 

የጋሠራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ተፈራ በበኩላቸው የወረዳው አርሶ አደር የዝናብ ውሃን ብቻ ጠብቆ ከሚያካሄደው የሰብል ልማት በተጓዳኝ በበጋውም ወቅት መስኖን በመጠቀም ስንዴንና ሌሎች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ በበኩላቸው በዞኑ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ወቅት ከ183 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል ። 

እስከ አሁን በተደረገው የሥራ እንቅስቃሴም ከ60 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ማልማት ተችሏል። 

የበጋ መስኖ ስንዴን ውጤታማ ለማድረግ 2ሺህ የሚሆኑ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች በረዥም ጊዜ ብድር በልማቱ ለተሳተፉ አርሶ አደሮች መሰራጨቱን እንዲሁ። 

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ወቅት በተለያዩ ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ ከሚገኘው ከ183 ሺህ ሄክታር ከሚበልጥ መሬት ከ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም