ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ታላቅ አየር ኃይል እየተገነባ ነው -ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 27/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥን ታላቅ አየር ኃይል እየተገነባ ነው ሲሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

ዋና አዛዡ ከቢሾፍቱ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር 90ኛ ዓመት የአየር ኃይል የምስረታ ቀን አከባበርን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።


 

በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ አየር ኃይል በየዘመናቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ አኩሪ ገድል መፈፀሙን ዋና አዛዡ ገልፀዋል።

አሁንም የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና የሕዝባችን መመኪያ የሆነ ተቋም እየተገነባ ነው ብለዋል።

"የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነት እና የአንድነት ምልክት "በሚል መሪ ሐሳብ 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብርም አስታውቀዋል።

የምስረታ ቀኑ በአቪዬሽን ኤክስፖ፣ በአየር ትርኢት እና በሌሎችም ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገልጿል።

የምስረታ ቀኑ ለሀገር፣ ለተቋም ብሎም ለቢሾፍቱ ከተማ እድገትና የገፅታ ግንባታ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ከተማውን በማስዋብና ሰላሟን በመጠበቅ ነዋሪዎች ንቁ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም