ቀጥታ፡

ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያላቸውን ፖሊሲዎች መተግበር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያላቸው ፖሊሲዎች መተግበር እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ተወካይና በኢትዮጵያ የክፍለ አህጉር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፈን ባይኖስ ገለጹ።


 

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ(POA)፣ በቻይና የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ እና የትብብር፣ የውይይትና የጥናት ማዕከል ትብብር የተዘጋጀው የቻይና አፍሪካ ስትራቴጂክ የትብብር ዓውደ ጥናት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የቻይና የሥራ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተለያዩ ዘርፎች ኮሚሽነሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ተወካይና በኢትዮጵያ የክፍለ አህጉር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፈን ባይኖስ፤ በአፍሪካ እና በቻይና መካከል ያለው አጋርነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የዩኒዶ ተልዕኮም ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ማስፈን መሆኑን ጠቁመው፤ ዘላቂነት ያለውን የኢንዱስትሪ ልማትን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ፖሊሲ ትግበራ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) የኢኮኖሚ አማካሪ አሊ ዘፋር በበኩላቸው፤ መድረኩ ከቻይናና አፍሪካ በተጓዳኝ የኃይል ልማት ትብብርን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ ልማት መሠረት መሆኑን አንስተው፤ ለመላው አፍሪካውያን የኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከ2025 እስከ 2030 ባለው ጊዜ 75 በመቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳካት ዒላማ መሰነቋን አውስተው፤ ከዚህ ውስጥ 95 በመቶው ከታዳሽ ኃይል የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም ኢትዮጵያን በታዳሽ ኃይል ግንባር ቀደም ከሆኑ ሀገሮች ተርታ እንደሚያሰልፋት ገልጸዋል።

ቻይና ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት የአፍሪካን የታዳሽ ኃይል ለማሳደግ አስተዋፅዖ ማድረግ እንደምትችል ጠቁመዋል።

የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን አብሮነት ማጠናከርና ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።


 

የቻይና ተነሳሽነት ከአፍሪካ ልማት ፍላጎት ጋር የተዛመደ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአብነትም የኃይል ዘርፉን የጠቀሱት ደግሞ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘላቂ ኢነርጂ ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ሳምሶን መክብብ(ዶ/ር) ናቸው።

ይህን የተቀመጠ ግብ ለማሳካት በኢንዱስትሪዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በመንግሥት የሚደረጉትን ሁሉንም ጥረቶች ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም