ቀጥታ፡

በክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም ተኪ ምርቶችና የተለያዩ ዘርፎችን የሚደግፉ ቴክኖሎጂዎች እየተመረቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦በክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም ተኪ ምርቶችና የተለያዩ ዘርፎችን የሚደግፉ ቴክኖሎጂዎችን እያመረቱ መሆኑ የፈጠራ ባለሙያዎች ገለጹ።

"ክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም" በሀገሪቱ ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና የሰው ኃይል ክህሎት ማጎልበትን በተመለከተ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካይነት የሚመራ ሀገራዊ ተነሳሽነት ነው። 


 

ይህ ፕሮግራም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን (TVET) ከዘመኑ የሥራ ገበያ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ወጣቶች ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል ያለመም ነው። 

የክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ብሩክ ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚችሉበት ምህዳር እየተፈጠረ ነው። 

በዚህም የግል ዘርፉና የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፎም እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በመስኩ የተሻለ አቅም እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ዜጎች በማሰባሰብ የሥልጠና፣ የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ ድጋፍ ከማመቻቸት ጨምሮ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።    

በመጀመሪያው ዙር ከ400 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው ከ80 በላይ ቴክኖሎጂዎች መመረታቸውን ተናግረው፤ በፕሮግራሙ ሁለተኛ ዙር በተኪ ምርቶች ላይ  152  ወጣቶች  99 ቴክኖሎጂዎችን እያለሙ ነው ብለዋል።       

በፕሮግራሙ በተሰጠው ድጋፍ በግብርና፣ ጤና፣ ደህንነት፣ አገልግሎት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል።  

ለአብነትም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በሰፋፊ እርሻዎች ላይ የውሃና ማዳበሪያ አጠቃቀምን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መተግበሩን ጠቅሰዋል።   

በኢትዮጵያዊያን የተመረቱ ቴክኖሎጂዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድሮች ላይም ከፍተኛ ውጤቶች መገኘታቸውንም አንስተዋል።   

በቴክኖሎጂና በተኪ ምርት ስራ ከተሰማሩት የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል ሄዋን አሊ፤ በክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም ባገኘችው ድጋፍ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመደራጀት ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን እያመረቱ መሆኑን ገልጻለች። 


 

የእንስሳት መኖ ማቀነባበር የሚያስችሉ አምስት መሳሪያዎችን ማምረት መቻላቸውንም ተናግራለች። 

ማቀነባበሪያው የእንስሳት ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርታለች። 


 

በሮቦቲክስና አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ የተሰማራው ወጣት ሁነኛው ዘሩ በበኩሉ የግብርናና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በሮቦት በመታገዝ ማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ መስራቱን ጠቅሷል። 

በሮቦቲክስና አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የስራ እድሎችን ለመፍጠር ከሌሎች ወጣቶች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።  


 

የፕላስቲክ ምርቶችን ማምረቻ መሳሪያ እያመረተ የሚገኘው አቤኔዘር ተከስተ፤ ማሽኑ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለቤት ውስጥ መገልገያ የሚውሉ ፕላስቲክ ምርቶች ለማምረት እንደሚያስችል ይናገራል።  

ይህም የፕላስቲክ ምርቶችን በመልሶ መጠቀም የስራ እድልን ለማስፋት እንደሚረዳም ገልፅዋል፡፡


 

በጤና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገችው ወጣት ነቢሃ ነስሩ፤  በጤና ተቋማት ተኝቶ ታካሚዎች አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልጉበት ወቅት የህክምና ባለሙያዎችን  በቀላሉ መጥራት እንዲችሉ እገዛ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ሰርታ በጤና ተቋም ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራች መሆኑን ጠቅሳለች።

ወጣቶች  የሚያጋጥሙ ችግሮችን ወደ እድሎች ለመቀየር መስራት ይኖርብናል ብላለች። 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም